በሐረሪ ክልል የጤና ተቋማትን የውስጥ ድርጅትን በማሟላት አገልግሎቱን ለማዳረስ እየተሰራ ነው

124

ሐረሪ፤ መስከረም 20/2015(ኢዜአ) ፡-በክልሉ ያሉ የጤና ተቋማትን የውስጥ ድርጅት በማሟላት የዘርፉን አገልግሎት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማዳረስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የሐረሪ ክልል ጤና ቢሮ ገለጸ።

ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶች በክልሉ ለሚገኙ የመንግስት ጤና ተቋማት ተሰራጭቷል።

የቢሮው ሃላፊ አቶ ያሲን አብዱላሂ እንደገለጹት፤ በተለይ የጤና ተቋማቱ ለማህበረሰቡ በሚሰጡት የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታየውን የህክምና ቁሳቁስ፣መድሃኒትና የጤና ባለሙያ ክፍተቶችን በማሟላት ረገድ  በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።

የተሰጠው ትኩረትም በክልሉ የሚገኙ ጤና ተቋማት ለማህበረሰቡ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል መሆኑን ተናግረዋል።

በቢሮው ግዢ ፣ ከጤና ሚኒስቴር፣ከኢትዮዽያ ህብረተሰብ  ጤና ኢንስቲትዮትና ከሌሎች ለጋሽ ድርጅቶች የተገኙና ግምታቸው ከ20 ሚሊየን ብር በላይ የሆኑ የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶችን በክልሉ ለሚገኙ ጤና ተቋማት ማሰራጨቱን ጠቅሰዋል።

የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶቹ የተሰራጩት በክልሉ ለሚገኙ ሁለት ሆስፒታሎች፣ለሐረር ደም ባንክና ላብራቶሪ ምርመራ፣ለሐረር ጤና ኮሌጅ እና ለ11 ጤና ጣቢያዎች  መሆኑን ኃላፊው አስረድተዋል።

በጤና ተቋማቱ ከተሰራጩት ቁሳቁሶች መካከል አልትራ ሳውንድ፣የደም መመርመሪያ ማሽን ፣የመኝታ አልጋዎች፣የላብራቶሪ መሳሪያዎችና መድሃኒት ማቀዝቀዣ ፊሪጆች እንዳሉበት ገልጸዋል።

የህክምና መሳሪያዎቹም ለእናቶችና ህጻናት እንዲሁም ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች  ህክምና ለመስጠት የሚያግዙ ናቸው ያሉት ደግሞ  የአሚር ኑር ጤና ጣቢያ ሃላፊ አቶ አብዱለዚዝ ሳሊህ ናቸው።

በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተጠቃሚ ለሆኑ ተገልጋዮች ጤና ተቋማቱ አገልግሎት አሰጣጣቸውን እንዲያሻሽሉ እንደሚየግዝ ተናግረዋል።

የሐረር ደም ባንክ ሃላፊ ወይዘሮ አረፋት መሃዲ በበኩላቸው፤ የህክምና መሳሪያዎቹ በተለይ ከደም ልገሳ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ለሚከናወኑ ስራዎች ጠቀሜታቸው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም