ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን ፈተናዎች ለማለፍ በምታደርገው ጥረት ሁሉ የኩባ ድጋፍ አይለያትም-በኢትዮጵያ የኩባ አምባሳደር ሆርጌ ሌፌብሬ ኒኮላስ

መስከረም 20/20115 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን ፈተናዎች ለማለፍ በምታደርገው ጥረት ሁሉ የኩባ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በኢትዮጵያ የኩባ አምባሳደር ሆርጌ ሌፌብሬ ኒኮላስ ተናገሩ።

የኢትዮ-ኩባ የህዝብ ለህዝብ ወንድማማችነት መድረክ ትናንት አዲስ አበባ በሚገኘው የኩባ ኤምባሲ ተካሂዷል።

በመድረኩም፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር ዓለሙ ስሜ፣ በኢትዮጵያ የኩባ አምባሳደር ሆርጌ ሌፌብሬ ኒኮላስ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካ  እና አውሮፓ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን፣ በኩባ  የኢትዮጵያ አምባሳደር ገነት ተሾመ እንዲሁም ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

በዚሁ ወቅት ንግግር ያደረጉት በኢትዮጵያ የኩባ አምባሳደር ሆርጌ ሌፌብሬ ኒኮላስ እንደጠቀሱት ኩባ ከአፍሪካ ጋር ጥልቅ ቁርኝት ያላት ሀገር ብትሆንም ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ወዳጅነት ልዩ ስፍራ ትሰጠዋለች።

ኢትዮጵያ የግዛት ሉዓላዊነቷን ለማስከበር ከሶማሊያ የዚያድባሬ ስርዓት ጋር በነበራት ውጊያ በርካታ ኩባውያን ተሳታፊ እንደነበሩ አውስተዋል።

ሁለቱ ሀገራት የረጅም ዘመን ወዳጅነታቸውን በሚያጠናክሩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የትብብር መስኮች ላይ እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን አሁናዊ ፈተናዎች  በራሷ አቅም በድል እንደምትወጣ እንገነዘባለን ያሉት አምባሳደሩ በዚሁ ሂደት የኩባ ድጋፍ እንደማይለያትም ተናግረዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር ዓለሙ ስሜ፤ ኢትዮጵያ  ከአፍሪካውያንና  ሌሎች ወዳጅ ሀገራት ጋር ያላትን ሁሉን አቀፍ ግንኙነት በማጠናከር ለጋራ ተጠቃሚነት እየሰራች ነው ብለዋል።

በኩባ ኤምባሲ የተካሄደው የወንድማማችነት ማጠናከሪያ መድረክም የዚሁ የትብብር አካል ነው ያሉት ዶክተር ዓለሙ ከኩባ ጋር ያለንን ታሪካዊ ወዳጅነትም የማይረሳ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያና ኩባ ወዳጅነት በቀላሉ የሚታይ ሳይሆን በደም አሻራ የታተመ  ነው ሲሉም ኩባውያን በካራማራ ከኢትዮጵያ ጋር በአንድነት በመሰለፍ  ያደረጉትን ተጋድሎ አንስተዋል።

መንግስት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓና አሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን በበኩላቸው፤ ኩባ በርካታ ጫናዎችን ተቋቁማ ካለፈችበት መንገድ ኢትዮጵያ ትምህርት እንደምትወስድ ገልጸዋል።

ኩባ በተለያዩ መስኮች ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም ወዳጅነቷን አስመስክራለች ያሉት አምባሳደር  እሸቴ፤ በቅርቡ  ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች የባለሙያዎች የምርመራ ኮሚሽን ያወጣውን ፍርደ ገምድል ሪፖርት በመቃወም ኩባ ግንባር ቀደም መሆኗን ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካና የወዳጅ ሀገራት የወንድማማችነት መድረክን በአዲስ አበባ በሚገኙ 13 የአፍሪካ ሀገራት  እንዲሁም በደቡብ ኮሪያና ኩባ ኤምባሲዎች  እያካሄደች ነው።

የወንድማማችነት መድረኩ እስካሁን በሱዳን፣ በአልጀሪያና በኩባ ኤምባሲዎች የተካሄደ ሲሆን በቀሪዎቹም ቀጥሎ እንደሚከናወን ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም