ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የሁለትዮሽ ትስስርና ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

አዲስ አበባ መስከረም 20 / 2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የሀገራቱን የሁለትዮሽ ትስስርና ግንኙነት ለማጠናከር መስማማታቸው ተገለጸ።

የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼህ መሀመድ በኢትዮጵያ የነበራቸውን የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ማጠናቀቃቸውን አስመልክቶ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የሁለቱ አገራት መሪዎች የጋራ ስምምነትን ይፋ አድርጓል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኢትዮጵያ  የመጀመሪያ የስራ ጉብኝት  ከመስከረም 28 እስከ 29  ቀን 2015 ያደረጉትን የሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሃሙድን ተቀብለው አነጋግረዋል።

መሪዎቹ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር ቁልፍ የጋራ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ቅድሚያ በሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ ለመስራት መስማማታቸው ተገልጿል።

ሁለቱ መሪዎች ከስምምነት ላይ የደረሱባቸው 10 ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸው

1. የሁለቱን አገራት እና ሕዝቦች ዘላቂ የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር እና በግዛት አንድነት እና ሉአላዊነት ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል

2. ጀግናው የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ለሶማሊያ ሰላም፣ በመረጋጋት እና አገር ግንባታ ለከፈለው ከፍተኛ መስዕዋትነት መሪዎቹ ያላቸውን አክብሮት ገልፀዋል

3. መሪዎቹ በሁለቱ አገራት የጋራ ጠላት በሆኑት ሽብርተኝነት እና ፅንፈኝነት ላይ የደህንነት ተቋማቶቻቸው በቅንጅት ተናብበው እንዲሰሩ እና የደህንነት መረጃ ለመለዋወጥ ተስማምተዋል።

4. ሁለቱም መሪዎች የሶማሊያ ጦር በሂራን እና ጋልሙዱግ አካባቢዎች በአሸባሪው አልሸባብ ታጣቂዎች ላይ ያስመዘገቡትን ድል አድንቀዋል።

5. መሪዎቹ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሶማሊያ ላይ ላለፉት 30 ዓመታት ጥሎት የቆየው የጦር መሳሪያ ግዢ ማእቀብ እንዲነሳ በጋራ ጥሪ አቅርበዋል፤ የማእቀቡ መነሳት ሶማሊያ የጦር ኃይሏን ለማደራጀትና በአሸባሪው አልሸባብ በኩል ያለባትን ስጋት በአግባቡ ለመቅረፍ ያስችላታል

6. ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት የጋራ ጥረታቸውን ሊያደናቅፉ የሚችሉ የውጭ ጣልቃ ገብነቶች ተጽዕኖዎችን መቀነስ እና ሽብርተኝነትን ውጤታማ በሆነ መንገድ መዋጋት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።ለዚህ ተጽዕኖም መደበኛ የሁለትዮሽ ምክክሮችን ለማካሄድና በባለብዙ ወገንና ክልላዊ ፎረሞች በጋራ ብሄራዊ ጥቅሞቻቸውን በጋራ ለማስቀጠል ተስማምተዋል።

7. ሁለቱ ሀገራትና ሰፊው ክፍለ ሀገር፣ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎች የክልሉን ህዝብ የኑሮ ውድነት እያሰጋ መሆኑን መሪዎቹ አንስተዋል፤ በዚህ ዙሪያ መተባበር አለመቻል እና እነዚህን ተግዳሮቶች ለማሸነፍ ጥረቶችን እንደገና ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አፅንዖት ሰጥተዋል። የረጅም ጊዜ የኑሮ መቋቋሚያ ግንባታን ጨምሮ ዓለም አቀፍ አጋሮች የተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን መደገፋቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

8. የሶማሊያ መንግስታዊ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞችን አቅም ለማሳደግ በኢትዮጵያ እየተሰጡ የሚገኙትን የትምህርት እድሎች አጠናክሮ ለመቀጠል ተስምተዋል።

9. ሁለቱ መሪዎች በተጠናከረ የፖለቲካና የፀጥታ ትብብብሮች በተጨማሪ በንግድ፣ በኢኮኖሚና በመሰረተ ልማት እንዲሁም በመገናኛ መስኮች ትብብርን ማስፋት አስፈላጊ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።

10. የሁለቱ ሀገራት የመንግስት መሰሪያ ቤቶች የጋራ የሚኒስትሮች በኮሚሽን እንዲያቋቁሙ መመሪያ ያወጡ ሲሆን በጋራ የጥቅም ጉዳዮች ላይ ለመወያየት እና አቅጣጫ ለማውጣት ተስማምተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም