ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የሰው ልጅ መገኛና ምድረ ቀደምትነት የሚያሳይ የተደራጀ ሙዚየም እንዲኖር ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል-ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ

መስከረም 19 /2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛና የሀገሪቱን ምድረ ቀደምትነት የሚያሳይ የተደራጀ ሙዚየም እንዲኖራት በትኩረት መሰራት እንዳለበት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።

ፕሬዝዳንቷ ይህን ያሉት የኢትዮጵያ የታሪክ ዘመን አርኪኦሎጂ ቋሚ አውደርዕይን በብሔራዊ ሙዚየም መርቀው ሲከፍቱ አውደርዕዩ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል የተሰባሰቡ ለህዝብ ዕይታ የቀረቡ ታሪካዊ ቅርሶችን መመልከታቸውን ተናግረዋል።

ቋሚ አውደርእይው የኢትዮጵያ እና የፈረንሳይ 125ኛውን አመት የዲፕሎማሲ ግንኙነት አስመልክቶ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ከፈረንሳይ የጥናት ማዕከልና በኢትዮጵያ የፈረንሳይ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ያደራጀው ነው።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ኢትዮጵያና ፈረንሳይ በባህል፣ በቅርስ ምርምር ዘርፍና በቱሪዝም ዘርፍ ያላቸውን ጠንካራ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን አንስተዋል።

ከታሪካዊ ግንኙነቱ በመነሳት በቀጣይ ቅርስ በማልማት ዙሪያ ብዙ መስራት እንደሚቻል ገልጸው የተከፈተው የታሪክ ዘመን አርኪኦሎጂ ቋሚ አውደርዕይ በአገራቱ መካከል ያለውን የጠበቀ የሁለትዮሽ ግንኙነት ማሳያ ነው ብለዋል።  

ፕሬዝዳንቷ ኢትዮጵያ የበርካታ ታሪክ ባለቤት ብትሆንም የተደራጀ ሙዚየም በማቋቋም በኩል ክፍተት እንዳለ ጠቅሰዋል። 

በመሆኑም በኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ ሙዚየም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ ይገባል ብለዋል። 

በአዲስ መልክ በተዘጋጀው ቋሚ አውደርእይ በታሪክና ባህል ከቅድመ አክሱም ዘመን ጀምሮ በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ያለውን ታሪክ የሚያሳይ ነው።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ኢትዮጵያና ፈረንሳይ በባህል፣ በቅርስ ምርምር ዘርፍና በቱሪዝም ዘርፍ ያላቸውን ጠንካራ ታሪካዊ ግንኙነት በዚሁ ጊዜ አንስተዋል።

የፈረንሣይ መንግስት ለቅርስ ጥበቃ እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋና በማቅረብ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ናሲሴ ጫሊ በበኩላቸው ላለፉተ 40 ዓመታት የኢትዮጵያን የታሪክ ዘመን አርኪኦሎጂ ስፋትና ጥልቀት የሚያሳይ አውደ ርዕይ ባለመኖሩ የኢትዮጵያን ታሪክ በተገቢው ሁኔታ ሳናሳውቅ ቀርተናል ብለዋል። 

በመሆኑም በአዲስ መልክ የተደራጀው የታሪክ አውደ ርዕይ ለጎብኝዎች ምቹና አስተማሪ መሆኑን ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያ የምትታወቅበትንና የቱሪዝም መሪ ቃል የሆነውን የምድረ ቀደምት ሙዚየም እውን ለማድረግ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሪሽ ሁለቱ አገሮች በቅርስ ጥበቃ ዘርፍ የቆየ ትብብሮች እንዳላቸው ጠቅሰዋል። 

በቀጣይም የፈረንሳይ መንግስት ሁለንተናዊ ትብብርና ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሪሽ ሁለቱ አገሮች በቅርስ ጥበቃ ዘርፍ የቆየ ትብብራቸውን ዘርዝረው በቀጣይም የፈረንሳይ መንግስት ሁለንተናዊ ትብብርና ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም