ቀጥታ፡

የባህር ዳር ከተማን እድገት የሚያፋጥኑና ህዝብን የሚጠቅሙ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ

ባህር ዳር (ኢዜአ) መስከረም 19/2015 የባህር ዳር ከተማን ሁለንተናዊ እድገት በማፋጠን የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የሚያሳድጉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው የተመሰረተበትን 60ኛ ዓመት በዓል አከባበር በማስመልከት ከከተማዋ ህብረተሰብ፣ ተቋማትና ሲቪክ ማህበራት ተወካዮች ጋር ዛሬ ተወያይቷል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ በመድረኩ ላይ እንዳሉት፣ ተቋሙ ከመማር ማስተማር፣ከምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ባሻገር የከተማዋን እድገት ለማፋጠን የሚያስችሉ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

"ባለፉት ዓመታት ባደረገው እንቅስቃሴም የከተማዋ እድገት እንዲፋጠንና ደረጃዋን የጠበቀች እንድትሆን የሚያግዙ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ተከናውነዋል" ብለዋል።

በቅርቡም ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ከ100 በላይ የተቋሙና የውጭ ባለሙያዎችን በማሳተፍ የከተማዋን መዋቅራዊ ፕላን አሰርቶ ለከተማ አስተዳደሩ ማስረከቡን በማሳየነት ገልፀዋል።

ፕላኑ የባህር ዳር ከተማን በማዘመንና ደረጃዋን በማሳደግ ለቱሪዝም፣ ለመኖሪያና ለኢንቨስትመንት ከተማ ተመራጭ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑንም ነው ያመለከቱት።

ዩኒቨርሲቲው ከመንግስትና ከአጋሮች በበጀትና በድጋፍ በዓመት በሚያገኘው እስከ 3 ቢሊዮን ብር የከተማዋን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚያፋጥንና ህብረተሰቡን በተለያየ መንገድ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎችን እንደሚሰራም አስረድተዋል።

ለከተማዋና የአካባቢው ማህበረሰብ ነጻ የትምህርት እድል እንደሚሰጥ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ በእዚህም ሰልጣኞች በሚያገኙት እውቀትና ክህሎት የራሳቸውንና የህብረተሰቡን ኑሮ እየለወጡ መሆኑን ተናግረዋል።

"የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅትም የንጽህና መጠበቂያዎችን አምርቶ ከማቅረብ ጀምሮ በፈለገ ጥበብ ሆስፒታል ግቢ የሕክምና ማዕከል በማቋቋም ማህበራዊ ሃላፊነቱን ተወጥቷል።" ብለዋል።

ባለፈው ዓመት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ንቁ ተሳትፎ በማድረግ በኢትዮጵያ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ግንባር ቀደም በመሆን መሸለሙን ዶክተር ፍሬው አስታውሰዋል።

ዶክተር ፍሬው እንዳሉት፣ ዩኒቨርሲቲው 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ሲያከብር እስካሁን የተጓዘባቸውን ሂደቶች ከህብረተሰቡ ጋር በመገምገም የቀጣይ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ በማሰብ ነው።

በዩኒቨርሲቲው የኢንፎርሜሽንና ስትራቴጅክ ኮሚኒኬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ዘውዱ እምሩ ባቀረቡት ጽሁፍ እንዳሉት፣ በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲው በ409 የትምህርት መርሃ ግብሮች ከ40ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ይገኛል።

ባሉት ዘጠኝ ግቢዎች 15 ተቋማትን እና አምስት የልህቀት ማዕከላትን በመመስረት እድገትን የሚያፋጥኑ የመርምር ስራዎችንና የሰለጠነ ሰው ሃይል እያቀረበ መሆኑንም አስረድተዋል።

"መድረኩ የከተማውና የአካባቢው ማህበረሰብ ተቋሙ ለከተማው እድገት እየተጫወተ ያለውን ሚና በአግባቡ ተገንዝቦ እንዲደግፍ ያግዛል" ብለዋል።

የአማራ ክልል ሽምግልና ስርዓት ማህበር አባል አቶ አለሙ ጥሩነህ በበኩላቸው "ለባህር ዳር ከተማ እድገት መፋጠን ዩኒቨርሲቲው እና የባህርዳር ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው" ሲሉ ገልጸዋል።

ልጆቻችንና የልጅ ልጆቻችን በዩኒቨርሲቲው ተምረው ለቁም ነገር የበቁት ተቋሙ በቅርበት በመኖሩ መሆኑን ጠቁመው፤ ለ60ኛ ዓመት አከባበሩ ንቁ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው የምስረታ በዓሉን በዓውደ ርዕይ፣ በዩኒቨርሲቲ ሳምንት፣ በእውቅና መርሃ ግብር፣ በውድድርና ተወዳዳሪነትን የሚያሳድጉ መርሃ ግብሮችን በማዘጋጀት እንደሚያከብር ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም