የግሸን ደብረ ከርቤን የንግስ በዓል ለማክበር ዝግጅት ተጠናቆ እንግዶች እየገቡ ነው --የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ - ኢዜአ አማርኛ
የግሸን ደብረ ከርቤን የንግስ በዓል ለማክበር ዝግጅት ተጠናቆ እንግዶች እየገቡ ነው --የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ

ደሴ፣ መስከረም 19/2015 (ኢዜአ) ለግሸን ደብረ ከርቤ ዓመታዊ የንግስ በዓል የቅድመ ዝግጅት ሥራው ተጠናቆ እንግዶች እየመጡ መሆኑን የደቡብ ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ኃላፊ አቶ መስፍን መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በዞኑ ከቱሪስት መስህቦች መካከል በየዓመቱ መስከረም 21 የሚከበረው ግሸን ደብረ ከርቤ የንግስ በዓል አንዱ ነው።
በዓሉ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ይዘቱን ጠብቆ በሰላማዊ መንገድ እንዲከበር የቅደመ ዝግጅት ሥራው ከወዲሁ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
በቅንጅት በተደረገ እንቅስቃሴ የውሃ፣ መንገድ፣ መብራትና የቴሌ አገልግሎቶችን ጨምሮ ሌሎች መሰረተ ልማቶች መስተካከላቸውን ተናግረዋል።
አቶ መስፍን እንዳሉት ከዚህ ሳምንት መግቢያ ጀምሮ በበዓሉ የሚታደሙ እንግዶች ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ እየገቡ ነው።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኮሮናቫይረስ እና አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት ምክንያት በዓሉ በሚፈለገው ልክ አለመከበሩን ያስታወሱት ኃላፊው፣ "ዘንድሮ በርካታ ምዕምናን በተገኙበት በተለየ መልኩ ይከበራል" ብለዋል።
በበዓሉ ላይ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ እንግዶች ይታደማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅና እንግዶችም ከወዲሁ እየገቡ መሆኑን ኃላፊው አስታውቀዋል።
አቶ መስፍን እንዳሉት በዓሉ የሚከበርበትን አካባቢ በማልማት የቱሪስት መዳረሻና የገቢ ምንጭ ለማድረግ ከሚደረገው ጥረት ባለፈ በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ እየተሰራ ነው።
"በዓሉ በሰላም እንዲከበር አጎራባች ዞኖችና ከተሞችን ያሳተፈ ቅንጅታዊ ሥራ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር እርገጤ ጌታሁን ናቸው።
ለፀጥታ ስጋት የሆኑ አካባቢዎች ተለይተው ስምሪት መሰጠቱን ጠቁመው፤ የበዓሉ ታዳሚዎች አጠራጣሪ ጉዳይ ሲመለከቱ ለፀጥታ አካላት ፈጥነው ጥቆማ እንዲሰጡ አሳስበዋል።
ምዕመናን በዓሉን በደስታና በድምቀት እንዲያከብሩ ባላድርሻ አካላትን ያሳተፈ ቅደመ ዝግጅት መደረጉንና በአሁኑ ወቅትም እንግዶች ወደ ግሸን እየገቡ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማሪያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መምህር አባ ለይኩን ወንድይፈራው ናቸው።
በበዓሉ ላይ ለመታደም ከመጡ እንግዶች መካከል አባ ሰውነት መለሰ በሰጡት አስተያየት፣ በዓሉ በደስታና በድምቀት እንዲከበር የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
ግሸን ደብረ ከርቤ ታላቅ ሃይማኖታዊ በዓል መሆኑን ጠቁመው፣ በእዚህ ታሪካዊ ቦታ በመገኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ግሸን ደብረ ከርቤ በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ ግማደ መስቀሉ ያረፈበት ቦታ ሲሆን በዓሉም በየዓመቱ መስከረም 21 ከፍተኛ ቁጥር ያለው ምዕመናን በተገኘበት በድምቀት ይከበራል።