ቀጥታ፡

ተጠያቂነት የሰፈነበት የፋይናንስ ሥርዓት በማስፈን የልማት ስራዎችን ለማፋጠን ይሰራል - የሲዳማ ክልል ፋይናንስ ቢሮ

ሀዋሳ ፤ መስከረም 19 / 2015 (ኢዜአ) በተያዘው የበጀት ዓመት በክልሉ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት የፋይናንስ ሥርዓት በማስፈን የልማት ስራዎችን ለማፋጠን እንደሚሰራ የሲዳማ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ገለጸ።

ቢሮው ከባለፈው የበጀት ዓመት የኦዲት ግኝት ውስጥ ከ26 ሚሊዮን ብር በላይ ማስመለሱ ተመላክቷል።

በሀዋሳ ከተማ ዛሬ በተካሄደው የሴክተሩ ክልል አቀፍ ጉባኤ ላይ  የቢሮ ሃላፊ ዶክተር አራርሶ ገረመው እንደገለጹት በተጠናቀቀው የስራ ዘመን ከ18 ቢሊየን ብር በላይ ለመደበኛና ካፒታል ፕሮጀክቶች መዋሉን ጠቅሰዋል።

በዘመኑ አብዛኛው ሀብት ለድህነት ቀናሽ ሴክተሮች ቅድሚያ እንደተሰጠ ጠቁመው፤ የፋይናንስ ስርዓቱን በማዘመን ሌብነትንና ብልሹ አሰራርን የሚጸየፍ አመራርና ሰራተኛ ለመፍጠር በተካሄደው እንቅስቃሴ አሰራር በጣሱ ባለሙያዎችና አመራሮች ላይ እርምጃ እንደተወሰደ ገልጸዋል።

በዚህም የክልሉን የፋይናንስ ስርዓት ማረጋጋት ተችሏል ያሉት ሃላፊው፤አገልጋይን የሚንከባከብና በአሰራር ልህቀት የሚያምን አመራርና ፈጻሚ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ2 ሺህ ለሚበልጡ ባለሙያዎች በፋይናንስና ፕሮጀክት አስተዳደር፣ በውስጥ ኦዲትና በግዥ ስርዓቱ አቅም የማጎልበት ስልጠና በመስጠት የፋይናንስ ስርዓቱን ለማዘመን ተሰርቷል ብለዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ከተደረጉ 163 የኦዲት ግኝቶች 46 ሚሊዮን ተመላሽ የሚደረግ ገንዘብ መገኘቱን ጠቅሰው ከዚህ ውስጥ 26 ሚሊዮኑ ማስመለስ መቻሉን  ጠቅሰዋል።

ቀሪዎቹ በህግ የተያዙና በሂደት ያሉ እንደሚገኙም ዶክተር አራርሶ አስረድተዋል።

በክልሉ የሚከናወኑ የልማት ስራዎችን የሚያፋጥኑ ተቋማዊ አሰራሮችን በመዘርጋት የፋይናንስ ስርዓቱ ግልጽና ተጠያቂነት የሰፈነበት ለማድረግ በቀጣይም  እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የብልጽግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ የብልጽግና ጉዞውን የሚያረጋግጡና የህዝቡን ኑሮ ሊቀይሩ የሚችሉ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ የተከናወኑ ስራዎች ውጤት እንደተገኘባቸው ተናግረዋል።

በፋይናንስ ሥርዓቱ የሚታዩ የአሰራር ጥሰቶችን የሚከታተል ግብረ ሃይል መኖሩን ጠቅሰው፤ የህዝብና የመንግስት ሃብት እንዳይባክን ለማድረግ ህጋዊ እርምጃ የመውሰዱ ሂደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ፋይናንስን ማስተዳደር የመንግስትና የህዝብን ሃብት በአግባቡ መምራት እንደሆነ የገለጹት ተሳታፊዎች መካከል  የዳራ ወረዳ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዳኛቸው ፈለቀ ናቸው፡።

በፋይናስ አስተዳደደር ሥርዓት የተሻለ አፈጻጻም ካስመዘገቡት መካከል አንዱ በሆነው ተቋማቸው በካፒታል ፕሮጀክቶች አፈጻጸምና የኦዲት ግኝቶችን በማስመለስ የተከናወነው  ስራ ውጤት እንደተመዘገበበት ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም