"ፒሲኢ ቬንቸር ማኑፋክቸሪንግ" በአዲስ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ያስገነባውን የቆዳ ውጤቶች ማምረቻ ፍብሪካ አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
"ፒሲኢ ቬንቸር ማኑፋክቸሪንግ" በአዲስ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ያስገነባውን የቆዳ ውጤቶች ማምረቻ ፍብሪካ አስመረቀ
መስከረም 19/2015 (ኢዜአ) "ፒሲኢ ቬንቸር ማኑፋክቸሪንግ"በአዲስ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ያስገነባውን የቆዳ ውጤቶች ማምረቻ ፍብሪካ አስመረቀ፡፡
ፋብሪካውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል መርቀው ከፍተዋል፡፡
ድርጅቱ ከዚህ ቀደም ስራው መጀመሩን ያስታወሱት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ በአሁኑ ወቅትም በአንድ ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪ የማስፋፊያ ፕሮጀክት መስራቱን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የቆዳ ውጤቶች ምርት በዓለም ገበያ እንዲተዋወቅ አምባሳደር ሆኖ እየሰራ ያለ ድርጅት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ድርጅቱ በተለይ ሴቶችን ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡
ድርጅቱ ሰፊ የስራ ዕድል ለመፍጠርና በቀጣይ አስር ዓመት ከዘርፉ እስከ አንድ መቶ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ወደ ገበያ ለማስገባት አቅዶ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ መንግስት የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
መንግሥት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን ለመደገፍ የፖሊሲ ማሻሻያዎችና የተለያዩ የድጋፍ ማዕቀፎችን በማከናወን ላይ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ካላት የእንስሳት ሀብት አንጻርም የቆዳው ዘርፍ ትኩረት ተሰጥቶ ከተሰራበት ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢያን በንትሌይ ድርጅቱ የኢትዮጵያ የቆዳ ምርቶችን በዓለም ገበያ ለማስተዋወቅ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ፋብሪካው በአጠቃላይ ከ200 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠሩንም አንስተዋል፡፡