የኦሮሞ ምርምር ማህበር መመስረት ትውልድን በእውቀት በመቅረጽ ሚናው የጎላ ነው--የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ

መስከረም 19/2015 (ኢዜአ) የኦሮሞ ምርምር ማህበር መመስረት ትውልድን በእውቀት በመቅረጽ ሚናው የጎላ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

የኦሮሞን ህዝብ ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋ እና የገዳ ስርዓት በእውቀት በመመርመር ሰንዶ ለትውልድ ማስተላለፍ ላይ ይሰራል የተባለው የኦሮሞ ምርምር ማህበር ምስረታ መርሃ ግብር ዛሬ በአዲስ አበባ ኢሊሊ ሆቴል ተካሂዷል።

ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ እንዳሉት የክልሉ መንግስት ከመሰረተ ልማት ግንባታ በተጓዳኝ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት ያለው የሰው ልጅ አዕምሮ ግንባታ ላይ ነው።

አሁን ያለውን ነባራዊ የዓለም ሁኔታ ከግምት በማስገባት በእውቀት የዳበረ ትውልድን ማፍራት እንደሚገባ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ለዚህ ስኬት ዛሬ የተመሰረተው የምርምር ማህበር የጎላ ሚና እንደሚኖረው አመለክተዋል።

የማህበሩ መመስረት እውቀትን በሙያና በጥናት በታገዘ ለማጎልበት ያግዛል ሲሉ ነው የጠቀሱት።

የክልሉ መንግስት ለማህበሩ የ50 ሚሊዮን ብር ድጋፍ በመነሻነት ማድረጉን ገልጸው ማህበሩ ለሚያካሄደው ያልተገደበ የጥናትና ምርምር ተግባሩ መንግስት ከጎኑ እንደማይለይም ቃል ገብተዋል።

የኦሮሞ ታሪክ፣ ባህልና ማሕበራዊ ጉዳዮች ላይ ጥናት በማካሄድና በመሰነድ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ማህበሩ የተመሰረተበት ዓላማ መሆኑን ያነሱት ከማህበሩ መስራች የቦርድ አባላት አንዱ የሆኑት የታሪክ ጸሐፊና ተመራማሪ አቶ ታቦር ዋሚ ናቸው።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት መካከል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት አማካሪ አቶ መሐመድ አህመድ እንዳሉት መሰል የጥናት ማህበራት የተደበቁ መልካም እሴቶችን ይፋ በማውጣት አብሮነት እንዲጠነክርና ትውልድ እንዲገነባ ያግዛሉ።

በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ሕግ መምህር ሮባ ጴጥሮስ በበኩላቸው "አገር ለመገንባት እና አብሮነትን ለማጠናከር የወል የሆኑ እሴቶችን በምርምር ታግዞ ማውጣት ይገባል" ነው ያሉት።

ለዚህ ደግሞ የምርምር ማህበራት ሚና ከፍተኛ መሆኑን በማጉላት።

በኦሮሞ አርቲስቶች ማህበር የሚዲያና ፕሮሞሽን ዘርፍ ሃላፊ አርቲስት ቀሮ ታመነ እንዳለው በመሰል ማህበራት የሚወጡ ትክክለኛ የምርምር ውጤቶች በተለይም ትውሉዱን ከማህበራዊ ሚዲያው ውዥንብር ነጻ ለማውጣት ያግዛሉ።

በማህበሩ ምስረታ መርሃ ግብሩ ላይ የፌዴራልና የክልል የሥራ ሃላፊዎች፣ የዘርፉ ተመራማሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ ባለሀብቶች፣ አባ ገዳዎችና ሃደ ሲንቄዎች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም