ቀደምት አባቶቻችን ያቆዩልንን የአብሮነትና የመተባበር እሴት እንዳይበረዝ እንጠብቃለን ----የሲዳማና ወላይታ ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
ቀደምት አባቶቻችን ያቆዩልንን የአብሮነትና የመተባበር እሴት እንዳይበረዝ እንጠብቃለን ----የሲዳማና ወላይታ ወጣቶች
ሀዋሳ መስከረም 19/2015 (ኢዜአ) በወላይታ እና ሲዳማ ብሔረሰቦች መካከል የቆየውን የመተሳሰብ፣ የመረዳዳትና የመተባበር እሴት በማስቀጠል ሊከፋፍሉን የሚሞክሩትን በአንድነት እንከላከላለን ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ወጣቶች ተናገሩ።
የወላይታ ዘመን መለወጫ “ጊፋታ” በዓልን በጋራ ሲያከብሩ ኢዜአ ያነጋገራቸው ወጣቶች እንዳሉት፣ አሸባሪው ህወሓት በስልጣን ላይ በነበረባቸው ዓመታት ሁለቱን ወንድማማች ህዝቦች እርስ በእርስ በማጋጨት ልዩነት ሲፈጥር ቆይቷል።
ህወሓት የሰልጣን ዕድሜውን ለማራዘም ሲል አንድ የነበረውን የኢትዮጵያ ህዝብ በብሔር፣ በጎሳና በዕምነት በመከፋፈል ሲያጋጭ ቢቆይም ቀድሞ የነበረ አብሮነት በቀላሉ ሊሸረሸር እንዳልቻለ ወጣቶቹ ተናግረዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል የወላይታ ብሔር ተወላጅ ወጣት ብሩህ ጴጥሮሰ “ሁለቱ ወንድማማች ብሔሮች ከቀደምት አባቶቻችን ጊዜ አንስቶ ተባብረውና ተረዳድተው በጋራ ኖረዋል" ብላለች።
ህወሓት በስልጣን ዘመኑ ቀደምት አባቶቻችን ተጋብተውና ተዋለደው በፍቅርና በመተሳሰብ ይኖሩ የነበረበትን የአንድነት እሴት ለማፍረስ ተግቶ ሲሰራ እንደነበር አስታውሳለች።
"በጠላት ሴራ ተጠልፈን ሳንወድቅ ፍቅራችን በልጦ ዛሬ በዓላችንን በጋራ ለማክበር ችለናል" ስትልም ገልጻለች።
“ትናንት ዛሬ አይደለም፤ የሚለያየንን ነገር ሲሰሩብን ነበር ነገር ግን አንድ ሆነን በአብሮነት ቆይተናል" ያለችው ወጣት ብሩህ፣ ከቀደምት አባቶቻቸው የተማሩትን አንድነት፣ ፍቅር፣ መቻቻልና አብሮነትን አጠናክሮ ለማስቀጠል ዝግጁነቷንን አረጋግጣለች።
ከወላጆቻችን የተማርነውን የአብሮነት እሴት ከማስቀጠል ባለፈ ከእኔነት ይልቅ እኛ ለሚለው ትኩረት በመስጠት ሰላምን በጋራ ማጎልበት እንደሚገባም ገልጻለች።
የሲዳማ ብሔር ተወላጅ የሆነውና በ”ጊፋታ” ስነስርዓት ላይ የታደመው ወጣት ተመስገን በበኩሉ፣ በበዓልም ሆነ በማንኛውም ጊዜ በአንድ ገበታ የሚበሉና በጋራ የሚኖሩ ህዝቦችን ለመከፋፈል ህወሓት ለዓመታት የተጠነሰሰው ሴራ መክሸፉን ገልጿል።
ወጣቱ እንዳለው ህወሓት በህዝቡ ውስጥ ልዩነትን በመፍጠር አንድነትን ለመበተን ቢሞክርም አዳፈነው እንጂ እስከመጨረሻው ሊያጠፋው አልቻለም።
ለጊዜው የተዳፈነ የመሰለው አብሮነትና ፍቅር ዛሬ አይሎ መውጣቱን የገለጸው ወጣቱ፣ "ለዓመታት በህወሓት የተሴረው ሴራ በህብረተሰቡ እንድነት ከሽፏል፤ በዓሉንም በጋራ አክብረናል" ብሏል።
"የሲዳማ ዘመን መለወጫ 'ፊቼ ጫምባላላ' በዩኔስኮ እንደተመዘገበው ሁሉ 'ጊፋታ'ም ተመዝግቦ በዓሉ ከእኛ ባለፈ የዓለም ህዝብ እንዲሆን ከሲዳማ ወጣቶች ጎን ቆመን በጋራ እንሰራለን" ብሏል።
"የወላይታ የዘመን መለወጫ በዓል ላይ በመገኘት በጋራ እንዳከበርነው ሁሉ በቀጣይ ይህን አብሮነትና አንድነት በማጠናከር የፊቼ ጫምባላላ በዓልንም በጋራ በማክበር አብሮነታችንን እናጠናክራለን" ሲልም ወጣቱ ተናግሯል።
ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ በረከት ቸርነት በበኩላቸው እንዳሉት፣ በወላይታ የዘመን መለወጫ በዓል ሁለቱ ህዝቦች ተቀራርበው ማየታቸውን መደሰታቸውን ገልጸዋል።
በመካከላቸው የነበረው ቁርሾ አስወግዶ ፍቅርን የተከለ ስነስርዓት በመሆኑ ፋይዳው የጎላ ነው፤ አብሮነቱ በአንድ ሰሞን የበዓል ጊዜ ብቻ እንዳይሆነና ዘላቂነት እንደኖረውም አበክረው አንደሚሰሩ አረጋግጠዋል
የወላይታ ብሔር የዘመን መለወጫ “ጊፋታ” በዓል በተለያዩ ስነስርዓቶች በወላይታ ዞን በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች በመከበር ላይ ይገኛል።