የፀጥታና ደህንነት ግብረ-ኃይል የኢሬቻ በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊው ቅድመ-ዝግጅት እንደተጠናቀቀ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የፀጥታና ደህንነት ግብረ-ኃይል የኢሬቻ በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊው ቅድመ-ዝግጅት እንደተጠናቀቀ ገለጸ
መስከረም 19 ቀን 2015 (ኢዜአ) የኢሬቻ በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊውን ቅድመ-ዝግጅት ማጠናቀቁን የፀጥታና ደህንነት ግብረ-ኃይል አስታወቀ።
የፀጥታና ደህንነት ግብረኃይል ከአባገዳዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመሆን የኢሬቻ በዓልን ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲከበር የተደረገውን ዝግጅት አስመልክቶ ውይይት አድርጓል።
በውይይቱም የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፤ በዘንድሮ የኢሬቻ በዓል ከኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎችና ከጎረቤት ሀገር በርካታ እንግዶች እንደሚታደሙ ተናግረዋል።
የፀጥታና ደህንነት ግብረ ኃይሉም ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ ሰፊ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን ለአባገዳዎች አብራርተዋል።
በዚህም በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ በቂ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
የጋራ ፀጥታና ደህንነት ግብረ ኃይሉ የዘመን መለወጫና የመስቀል ክብረ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ መስራቱን አስታውሰው፤ በዚህም የፀጥታ ስጋት ለመፍጠር የተደረጉ ሙከራዎችን ከህዝብ ጋር በመቀናጀት መከላከል መቻሉን ገልጸዋል፡፡
አባ ገዳዎች ህብረተሰቡን የሚያስገነዝብ ሥራ ማከናወናቸውን አድንቀው፤ ኀብረተሰቡ አጠራጣሪ ነገሮችን ሲመለከት ለፀጥታ ኃይሉ መጠቆም እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡
በዓሉ ለሀገራችን የሰላም መልዕክት የሚተላለፍበት ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁላችንም የሚጠበቅብንን ልንወጣ ይገባል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ አባገዳዎች በበኩላቸው በኢሬቻ በዓል በርካታ ህዝብ የሚሳተፍበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በሰላምና በአብሮነት እንዲከበር ሁላችንም ኃላፊነታችንን መወጣት አለብን ብለዋል።
የፀጥታና ደህንነት ግብረኃይሉ በዓሉ በሰላማዊ ሁኔታ እንዲከበር በቂ ዝግጅት ማድረጉን ተመልክተናል ያሉት አባገዳዎች፥ የታችኛው የፀጥታ መዋቅር ከኀብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በተለይ በእንግዶች ላይ እንግልት እንዳይደርስ መተባበርና በተገቢው ሁኔታ ማስተናገድ እንደሚገባም ገልፀዋል።
በዓሉ የመላው ኢትዮጵያውያን የሰላምና የወንድማማችነት በዓል ሆኖ እንዲከበር ሁሉም የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባም ነው ያነሱት፡፡
የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሁሴን ፋይስ ኢሬቻ የምስጋና፣ የሰላም፣ የእርቅ እና የይቅርታ በዓል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የፀጥታና ደህንነት ግብረኃይሉ ከዚህ ቀደም ኢሬቻ በዓል ያለምንም ችግር እንዲከበር ማድረጉን አስታውሰው፤ ዘንድሮም በዓሉ በሰላም እንዲከበር ከፎሌ፣ ከቄሮና ከአባገዳዎች አደረጃጀት ጋር ውይይት በማድረግ ወደ ሥራ ተገብቷል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚፈልጉ ኃይሎች የፍቅርና የምስጋና በዓል የሆነውን ኢሬቻ ለጥፋት ተልዕኳቸው ማስፈጸሚያ እንዳያደርጉት አባገዳዎችና መላው ህዝብ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር መሥራት እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በተለይ አባገዳዎች በባለቤትነት መሥራት እንዳለባቸውም ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡
የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር መሃመድ አህመድ፤ በዓሉ በሰላም እንዲከበር የክልሉ የጸጥታ መዋቅር ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት እየሰራ ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡