በምዕራብ ኦሮሚያ የተለያዩ ዞኖች በበጋ መስኖ ስንዴ የተሻለ ምርት ለማግኘት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ኦሮሚያ የተለያዩ ዞኖች በበጋ መስኖ ስንዴ የተሻለ ምርት ለማግኘት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው
ጊምቢ/መቱ/ነቀምቴ መስከረም 19/2015/ኢዜአ/---በምዕራብ ኦሮሚያ የተለያዩ ዞኖች በበጋ መስኖ ስንዴ የተሻለ ምርት ለማግኘት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ዞኖቹ ገለጹ።
በምዕራብና ደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ የሚገኙት ምዕራብ፣ ምስራቅና ቄለም ወለጋ እንዲሁም ኢሉባቦር ዞኖች በበጋ መስኖ ስንዴ የተሻለ ምርት ለማግኘት ዝግጅት ላይ መሆናቸውን አንስተዋል።
በምዕራብና ቄለም ወለጋ ዞኖች ብቻ ከ70 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በመስኖ ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ ነው።
በሁለቱም ዞኖች ከሚለማው 70 ሺህ ሔክታር መሬት ከ3 ሚሊየን ኩንታል በላይ ስንዴ ለማግኘት ግብ ተጥሎ እየተሰራ እንደሚገኝም ተገልጿል።
የምዕራብ ወለጋ ዞን የመስኖ ልማት ጸህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብሬ አበራ እንደተናገሩት በዞኑ 35 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለመሸፈን ታቅዶ አየተሰራ ነው።
ከዚህም ከአንድ ሚሊየን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
ሂደቱ ውጤታማ እንዲሆን የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ በስፋት ተግባራዊ ለማድረግ አቅጣጫ መቀመጡን ጠቅሰው በአማካይ ከአንድ ሔክታር 38 ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን አንስተዋል።
የሚያስፈልጉ ግበዓቶች ለአርሶ አደሩ እየተከፋፈለ መሆኑን ተናግረው ከዚህም ውስጥ 759 የውሃ መሳቢያ ፓምፖች መዘጋጀቱንም ተናግረዋል፡፡
በቄለም ወለጋ ዞንም በበጋ መስኖ ለማረስ ከታቀደው ውስጥ 35 ሺህ ሔክታር በስንዴ በመሸፈን ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዷል።
የዞኑ የግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኦልብራት ሁንዴሳ በዚህ ወቅት ከሚያስፈልጉ ግብዓቶች መካከል ከ85 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር መዳበሪያና ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ እየቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ከ1 ሺህ በላይ የውሃ መሳቢያ ፓምፖች መዘጋጀታቸውን ገልጸው በመስኖ ልማት ስራውም ከ120 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እንደሚሳተፉም ገልፀዋል፡፡
በተመሳሳይ በኢሉባቦር ዞን በበጋ መስኖ ልማት የተሻለ ውጤት ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አስጨናቂ አድማሱ ተናግረዋል።
ለዚህ ስራ ስኬታማነት ደግሞ በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች ለሚገኙ ባለድርሻ አካላት የግንዛቤ መፍጠሪያ የንቅናቄ መድረኮችን ጨምሮ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ተከናውነው ወደስራ መገባቱን አንስተዋል።
በዞኑ በመስኖ ለማልማት ከታቀደው የስንዴ ምርት ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው የገለፁት።
የምስራቅ ወለጋ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት የአዝርዕት ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ፈንታ አሰበ እንዳስታወቁት በበጋ ወራት በዞኑ በሚገኙ 17 ወረዳዎች 35 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዷል።
በበጋው የስንዴ የመስኖ ልማት 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት ለማምረት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው በመስኖ ልማቱ 41 ሺህ የዞኑን አርሶ አደሮች ተሳታፊ ይሆናሉ ብለዋል።
በግብርና ስራው ወጣቶችን በማደራጀት በሰብል ልማት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በቡና ችግኝ ልማት እና በሌሎች የሥራ መስኮች ለማሰማራት አስፈላጊውን ዝግጅት መድረጉንም ገልጸዋል፡፡
የዞኖቹ አርስ አደሮችም በመንግስት በኩል እየተደረገላቸው ያለው ድጋፍ የተሻለ በመሆኑ በመስኖ ስራው ለመሰማራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የመስኖ ልማት ለአርሶ አደሮች የኑሮ መሻሻል አስተዋጾው የጎላ መሆኑን የተናገሩት አርሶ አደሮቹ በግብርና ስራው ለመሰማራት ከፍተኛ ተነሳሽነት እንዳላቸውም አክለዋል።
በግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ ታግዘው እየሰሩ መሆናቸውንና ከአካባቢያቸው አርሶ አደሮች ጋር በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ ውጤታማ ለመሆን ተስፋ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።
ከአንድ ሄክታር መሬት ላይ ባለፈው ዓመት ካገኙት በላይ የተሻለ ምርት ለማግኘት መዘጋጀታቸውን ነው የተናገሩት።