ኢትዮጵያ እና ሞሮኮ በወደብ፣ ተርሚናልና ሎጂስቲክስ ዘርፍ በትብብር ለመስራት ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ሞሮኮ በወደብ፣ ተርሚናልና ሎጂስቲክስ ዘርፍ በትብብር ለመስራት ተስማሙ
መስከረም 19 ቀን 2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ እና ሞሮኮ በወደብ፣ ተርሚናልና ሎጂስቲክስ ዘርፍ በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ።
በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ምህረቱ ማሞ የተመራ እና የኢትዮጵያ ባህርና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሮባ መገርሳንና ሌሎች የስራ ሀላፊዎችን ያካተተ ልዑክ በሞሮኮ የስራ ጉብኝት እያደረገ ይገኛል።
በጉብኝቱም የሞሮኮ ወደብ፣ ተርሚናልና ሎጂስቲክስ ዘርፍ ላይ ያሉ እንቅስቃሴዎችን መጎብኘታቸው ተገልጿል።
በጉብኝቱም ከሞሮኮ የወደብ፣ ተርሚናልና ሎጀስቲክስ ተቋም ሀላፊ መህዲ ታዚ ሪፊ ጋር በደረቅ ወደብ ልማት እና አገልግሎት እንዲሁም የኢትዮጵያ ሎጂስቲክስ አገልግሎት ዘርፉን ለማሳደግ በጋራ መስራት በሚቻልባቸው ዕድሎች ዙሪያ ተወያይተዋል።
ከውይይቱ መጠናቀቅ በኋላም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ከሞሮኮው አቻ ተቋም ጋር በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ በዘርፉ በትብብር መስራት እና መዋዕለ ነዋይ ማፍሰስን የሚያጠቃልል ሲሆን በኢትዮጵያ የባህርና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ስር የሚገኘውን የቃሊቲ ደረቅ ወደብ እና ተርሚናል የተሟላ አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን የደረጃ ማሳደግን በጋራ መስራትን ያካተተ መሆኑን ከባህርና ሎጀስቲክስ አገልግሎት የተገኘው መረጃ አመልክቷል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤