ቀጥታ፡

የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ኢትዮጵያ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎችን ያከናወነችበት ነበር- ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

መስከረም 19 ቀን 2015(ኢዜአ) 77ኛው የመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ኢትዮጵያ ስኬታማ ስራዎች ያካሄደችበት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ በመንግስታቱ ድርጅት 77ኛ ጠቅላላ ጉባዔ የተሳተፈው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራው ልዑክ የነቃ ተሳትፎ አድርጓል ብለዋል።

ልዑኩ ተልዕኮውን በስኬት አከናውኖ ተመልሷል ያሉት አምባሳደሩ የ2030 የዘላቂ ልማት ግብ በኮቪድ 19 ተፅዕኖ የደረሰበት በመሆኑ እሱን ለመታደግ ያተኮረ እንደነበር አንስተዋል።

ጉባኤው ዓለምን ለአደጋ የዳረጉ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እያሉና ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ ዳግም አስቸጋሪ ፖለቲካዊ ችግር ባለበት ወቅት የተደረገ ነው ብለዋል።

በጉባኤው ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እንዲሁም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ንግግሮች መደረጋቸውን አንስተዋል።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ትምህርትን በተመለከተ ስኬታማ ንግግር ስለማድረጋቸው ነው የገለጹት።

አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው የኢትዮጵያን የፖሊሲ አቅጣጫ በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን በሰሜን ኢትዮጵያ፣ ታላቁ የሕዳሴ ግድብና ዓለምአቀፋዊ ጉዳዮች የጋርዮሽ መፍትሔ ላይ ያተኩረ ንግግር አድርገዋል ነው ያሉት።

ከዓመታዊ ጉባኤው ጎን ለጎንም በሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ከ20 በላይ አገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች ጋር ውጤታማ ምክክርና ውይይት ስለማድረጋቸው አንተስተዋል።

የኢትዮጵያ ገፅታ ለመገንባት እና ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታን ለማስረዳት በአንድ ቦታና ጊዜ በማስረዳት የተሻለ ዕድል ያለበትና ተወያዮችም ከኢትዮጵያ ጎን ሆነው እንደሚደግፉ ያረጋገጡት አጋጣሚ እንደነበር ገልጸዋል።

በአረንጓዴ አሻራ ክንውንና ሁለንተናዊ ፋይዳ በስፋት የሚያስተዋውቅ እና የሰቆጣ ቃልኪዳን ላይ ሁለት መድረኮች በኢትዮጵያ በኩል ስለመዘጋጀታቸውና ጥሩ ውይይቶች መደረጉንም ተናግረዋል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር እና የሰቆጣ ቃልኪዳን ከኢትዮጵያ አልፎ ለተቀረው ዓለም ምሳሌ የሚሆኑ ስራዎች እንደሆኑ በብዙ ወገኖች ተነስቶ ኢትዮጵያ ትልቅ አድናቆት ተችሯታል ብለዋል።

የፕሬዝዳንት ሐሰን ሸክ ሞሐመድ ጉብኝትም ሰፊ ድንበር የሚጋሩት ሁለቱ አገራት የሁለትዮሽ ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በሚያጠናክር አግባብ የተደረገ መሆኑንና በመሪዎች ውይይት በሰላምና በልማት በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን ገልፀዋል።

የሁለቱ አገራት መሪዎች ህዝብን መሰረት ያደረገ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰሩና ሽብርተኝነት በጋራ ለመከላከል እንደሚሰሩ ስለመስማማታቸው ነው ያነሱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም