የኮሚሽኑ ሪፖርት በኢትዮጵያ ተላላኪ መንግስት ለማቋቋም ሲፈጸም የነበረን ድርጊት ገሀድ ያወጣ ነው--የጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ ምሁራን

121

ጅግጅጋ  መስከረም 18/2015 (ኢዜአ) የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት የኤክስፐርቶች ኮሚሽን በኢትዮጵያ ላይ በቅርቡ ያወጣው ሪፖርት አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራት ጫና በመፍጠር እነሱ የሚዘውሩት መንግስት ለማቋቋም ሲፈጽሙት የነበረውን ድርጊት ገሀድ ያወጣ ነው።

ሪፖርቱ ተቀባይነት የሌለው እና የተቋሙን ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ከመሆኑ ባለፈ ዓለም አቀፍ የጥናት መስፈርቶችን ያላሟላ መሆኑንም ምሁራኑ ተናግረዋል።

ዲፕሎማቶችን ጨምሮ በውጭና በሀገር ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የሪፖርቱን አድሎአዊነትና  የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም በማስረዳት ሀገር በነፃነቷ ፀንታ እንድትጓዝ ርብርብ እንዲያደርጉም አሳስበዋል።

በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሣይንስና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ትምህርት መምህራን የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሚፍታህ መሐመድ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ አሸባሪው ህወሓት በ27 ዓመታት የአገዛዝ ዘመኑ በዜጎች እና በሀገር ላይ ታሪክ የማይሽረው ዓለምአቀፍ ወንጀሎችን ጭምር ፈፅሟል።

"ሀገራዊ ለወጡን ተከትሎም ይህንኑ ክፉ ድርጊቱን በዜጐች እና የሀገር መከታ በሆነው የመከላከያ ሠራዊት ላይ በመድገም በአገር ላይ ማህበራዊ እና ምጣኔሃብታዊ ቀውሶችን ፈጥሯል" ሲሉም ገልጸዋል

ይህም ሆኖ መንግስት ሀገርን ለማዳን ያስተላለፈውን ተደጋጋሚ የሠላም ጥሪ ወደጎን ብሎ ለሦስተኛ ጊዜ ጦርነት በማካሄድ በዜጎች እና በአገር ላይ ዳግም ጥፋት እየፈጸመ መሆኑን ነው ያስረዱት።

"የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኤክስፐርቶች ኮሚሽን በሀገርና በዜጎች ላይ ሽብር እና ወንጀል እየፈጸመ ለሚገኘው ቡድን የወገነና ከእውነት ያፈነገጠ ሪፖርት ሰሞኑን በአገራችን ላይ ማውጣቱ ተቀባይነት የሌለው፤ የተቋሙንን ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ነው" ሲሉም ረዳት ፕሮፌሰር ሚፍታህ ተናግረዋል።

የወጣው ሪፖርት አንዳንድ ምዕራባውያን በአገራችን ላይ ጫና በመፍጠር በኢትዮጵያ እንደፈለጉ የሚዘውሩት መንግስት ለማቋቋም የተጓዙበት የተለመደ ድርጊታቸውን ገሃድ ያወጣ መሆኑንም ሙሁሩ አስረድተዋል።

እንደ ምሁሩ ገለፃ ሚዛናዊ ያልሆነውን ይህን የኮሚሽኑን ሪፖርት ሙሁራን፣ ዲፕሎማቶች፣ አክቲቪስቶች እና በየደረጃው ያሉ የማህበረሰብ ክፍሎች ተቀናጅተው እውነቱን ለዓለም ማህበረሰብ በማሳወቅ የአገርን ነፃነት ማፅናት ይገባቸዋል።

በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል መምህር ሙክታር ዑስማን በበኩላቸው፣ ዓለምአቀፍ የጥናት መስፈርት ሳይከተል የተዘጋጀው ሪፖርት በኢትዮጵያ ላይ ፖለቲካዊ ጫና ለመፍጠር ያለመና የከሸፈ ጥናት መሆኑን ገልፀዋል።

በተለይ ሪፖርቱ የኢትዮጵያ መንግስት ለዘላቂ ሠላም ሲል ያደረገውን ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ አንዲሁም ሰብአዊ ድጋፍ ወደትግራይ እንዲገባ ያደረገውን ጥረት ከመካድ ባለፈ ወገንተኝነቱን በአደባባይ ያንፀባረቀ መሆኑን አስረድተዋል።

ህወሓት በተለያዩ አካባቢዎች ያደረሰውን ዘርፈ በዙ ጉዳት ያላካተተና ሚዛናዊ ያልሆነ ሪፖርት በመሆኑ በየትኛውም መስፈርት ተቀባይነት እንደማይኖረውም መምህሩ ገልጸዋል።

"ድርጅት ከሊግ ኦፍ ኔሽን ጀምሮ እስከ ሕዳሴ ግድብ ድረስ ኢትዮጵያን በመካድ እና ጫና በመፍጠር ተደጋጋሚ በደሎች የፈፀመ በመሆኑ ከእሱ ሚዛናዊ ጥናት እና ውጤት አይጠበቅም" ነው ያሉት።

በመሆኑም ይህን የሐሰት ሪፖርት በተቀናጀ መንገድ በማጋለጥ በአገሪቱ የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ የእድገትና የለውጥ ጉዞ ለማሳካት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ መምህር ሙክታር አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም