በቁርጥ ቀን ኢትዮጵያን ያገለገለ የጥበብ ሰው

114

በኪነ-ጥበቡ ዘርፍ  በአጭር ጊዜ ታላቅ ስም ያተረፈው ከያኒ ይህችን ምድር ሲቀላቀል ወላጆቹ “ተገኔ” የሚል ስም አወጡለት።

በወላጆቹ የወጣለት ስም መጠሪያ ሆኖ ያገለገለው እስከ ዘጠኝ ዓመቱ ብቻ ነበር። ገና ከህፃንነቱ በሙዚቃ ፍቅር የወደቀው ታዳጊ በወቅቱ በጦሩ 603 ኮር ሥር በተቋቋመው የሙዚቃ ቡድን መድረክ ላይ ተከስቶ በሚስረቀረቅ ድምፁ መዝፈኑን ተከትሎ በሠራዊቱ ዓይንና ልብ ውስጥ ገባ።

የታዳጊውን አዘፋፈን የተመለከቱት ወታደራዊ ኃላፊዎች ለሙዚቃ ቡድኑ የተገባ ታዳጊ ነው በማለት በወር 120 ብር እየተከፈለው በድምፃዊነት እንዲቀጠር አደረጉት።

በካምፑ የሠራዊት አባላት የ“ተገኔ” መጠሪያ ስም ተቀይሮ ታዳጊው ድምፃዊ “ማዲንጎ” በሚል ስያሜ መጠራቱን ቀጠለ።

የማዲንጎ መጠሪያም ከካምፕ አልፎ በወላጆቹ ብሎም በሚያውቁት ሁሉ ተቀባይነት አግኝቶ የስሙ መጠሪያ ሆኖ አብሮት ዘልቋል።

የኤፍሬም ታምሩ፣ ኤሊያስ ተባባል፣ ሙሉቀን መለሰ፣ መሀሙድ አህመድ እና ሌሎችንም ድንቅ ሙዚቀኞች ሥራ በመድረክ ላይ  ይዞ በመቅረብ አድናቆትን ያተረፈው ማዲንጎ አፈወርቅ የሙዚቃ ህይወቱ በእጅጉ እያደገ መጥቶ የራሱን ሥራዎች በመሥራትም በኢትዮጵያ ሙዚቃ ትልቅ አሻራ ማሳረፍ ቻለ።

በተለይም የአገርን ፍቅር፣ ክብርና ልዕልና ከፍ የሚያደርጉ የተዋቡ ጣዕመ ዜማዎችን ለሕዝብ በማድረስ ታላቅ ሙዚቀኛ መሆኑን ያስመሰከረው ማዲንጎ አፈወርቅ በ“ስያሜ አጣሁላት” የተጀመረው የራሱ ሥራ ለሌሎች ተወዳጅ ሥራዎቹ መንደርደሪያ ሆኖታል።

ከለጋነት እድሜው ጀምሮ የአገሩን ክብርና ታላቅነት በጥበብ እየቃኘ በመረዋ ድምፁ ያቀነቀነው ማዲንጎ የበርካቶችን ቀልብ በመግዛት በኢትዮጵያ በእጅጉ ተወዳጅ ከሚባሉ አርቲስቶች መካከል በግንባር ቀደምትነት እንዲቀመጥ አድርጎታል።

አርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ ኢትዮጵያ በፈለገችበት አጋጣሚ ሁሉ አለሁ በማለት ቀድሞ የሚገኝ፤ ለአገሩ የማይሰስት፣ የወታደርን ህይወት በጥበብ አብሮ በመዝመት ከልጅነቱ ጀምሮ ጠንቅቆ የሚያውቅ ለአገሩ ብዙ ዋጋ የከፈለ የጥበብ ሰው ነው።

አዲስ አበባ ከእርጎዬዎች፣ ላፎንቴኖች እንዲሁም ሌሎች ጋር በመሆን በምሽት ቤቶችና “ዜማ ላስታስ” ባንድ በመቀላቀል በመድረክ ይሰራቸው በነበሩ ሙዚቃዎች የበርካቶችን አድናቆት አግኝቷል።

በራሱ ሥራዎችም በ“ስያሜ አጣሁላት የጀመረው የሙዚቃ ህይወቱ አይደረግም፣ ስወድላት፣ ጎንደር፣ አንበሳው አገሳ፣ ማህሌት፣ አማን ነው ወይ ጎራው፣ ጎዳናው፣ እባክሽ ታረቂኝ፣ ከተለያየን” እና በሌሎችም የጥበብ ሥራዎቹ የአገሩንና የሕዝቡን ፍቅር ገልጾበታል።

በትዝታ ቅኝቱ “እገነባለሁ እንጂ ድካሙ ቢያመኝም፤ ለፈረሰው ቤቴ ሳለቅስ አልገኝም” እያለ ባቀነቀነበት ሥራው በእጅጉ ተወዳጅ ለመሆን በቅቷል ማዲንጎ።

በጦሩ ውስጥ ገብቶ ከለጋነት እድሜው ጀምሮ አገሩን ማገልገል የጀመረው ማዲንጎ በወቅቱ በነበረው የሥርዓት ለውጥ የሠራዊቱ የሙዚቃ ቡድን ቢፈርስም እርሱ ግን ከጎንደር እስከ ባህርዳር ከዚያም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በሙዚቃ ህይወቱ በተወዳጅነት ዘልቋል።

በቁርጥ ቀን ኢትዮጵያን እያገለገለ የኖረው የጥበብ ሰው አሸባሪው ህወሓት የአገርን ህልውና አደጋ ላይ በጣለበት አጋጣሚ ወደ ለመደበት የሠራዊት ካምፕ አምርቶ በጥበብ ሥራዎቹ ሠራዊቱን ለማነቃቃት ጊዜ አልፈጀበትም።

በወታደራዊ ማሰልጠኛ ጣቢያዎች በመገኘት ምልምል ወታደሮችን “የሞራል ስንቅ ማስታጠቅ የቻለ” ታላቅ የአገር ባለውለታ ነው።

በኢትዮጵያ ህልውና ጉዳይ መቼም ቢሆን ወደ ኋላ የማያውቀው ማዲንጎ አፈወርቅ ከዘፈኑም ባለፈ በአገሩ ጉዳይ “አይደረግም” የሚል አቋም በመያዝ በጥበብ ሥራዎቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ ነግሶ የኖረ ከያኒ መሆኑ ይታወቃል።

ለአገሩ ለመሥራትና ለማገልገል ታከተኝ የማያውቀው ማዲንጎ አሁን ላይ ግን የረዥም ጊዜ ህልሙ ተገትቶ፤ "ሩቅ ዓላሚ-ቅርብ አዳሪ" ለመሆን ተገዷል።

ኢትዮጵያ ሁልጊዜም አለሁልሽ የሚላትን የቁርጥ ቀን ልጇን በድንገት አጥታዋለች። ለአገሩና ለሕዝቡ ገና ብዙ ለማገልገል ተዘጋጅቶ የነበረው ማዲንጎ በትናንትናው እለት በድንገት ከቤቱ እንደወጣ ሳይመለስ ቀርቷል።

በአገር ባለውለታውና በተወዳጁ ድንገተኛ ህልፈት በርካቶች ሐዘናቸውን የገለጹ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ “ለአገሩ በአጭር እድሜው ብዙ የሠራ ከያኒ፤  ሀገር በተደፈረች ጊዜ ሕመሙን እየቻለ ግንባር ተገኝቶ ሠራዊቱን ያጀገነ፤ ሠልጣኞችን ያበረታ መሆኑን በመግለጽ በአርቲስቱ ህይወት ማለፍ የተሰማኝ ሐዘን ከባድ ነው" በማለት ገልጸዋል።

የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደኅንነት አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል ተመስገን ጥሩነህ ሌሎችም ሚኒስትሮችና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በአርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልጸዋል።

በርካታ የጥበብ አፍቃሪዎችና አድናቂዎቹም በአርቲስቱ ድንገተኛ ህልፈተ-ህይወት ሐዘናቸውን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።

በትናንትናው እለት ህይወቱ ያለፈው ተወዳጁ ድምፃዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ሐሙስ መስከረም 19 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ 6 ሰዓት በወዳጅነት አደባባይ የክብር ሽኝት ተደርጎለት ሥርዓተ ቀብሩ ከቀኑ 10 ሰዓት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይፈጸማል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም