የአደባባይ በዓላትን በጋራ ማክበራችን ለትብብር፣ አንድነትና አብሮነታችን መጠናከር ፅኑ መሰረት የሚያኖር ነው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

63

መስከረም 18 ቀን 2015 (ኢዜአ)  የአደባባይ በዓላትን በጋራ ማክበራችን ለትብብር፣ ኢትዮጵያዊ አንድነትና አብሮነታችን መጠናከር ፅኑ መሰረት የሚያኖር ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

የፊታችን ቅዳሜ እና እሑድ በአዲስ አበባ እና ቢሾፍቱ የሚከበረውን የኢሬቻ በዓል በማስመልከት ለአራት ቀናት የሚቆይ ባዛርና ኤግዚቢሽን በአዲስ አበባ ተከፍቷል።

ኤግዚቢሽንና ባዛሩን በይፋ ያስጀመሩት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የዘመን መለዋጫ፣ የደመራና የመስቀል በዓላት በህብረ-ብሔራዊነት፣ በመከባበርና በመተሳሰብ የበዓሉን ትውፊት ከፍ ባደረገ መልኩ መከበሩን አስታውሰዋል።

የበዓላት መከበር ለገቢ ማደግ፣ የቱሪዝም መስህብነት መጨመርና ለእርስ በርስ መስተጋብር መጠናከር ጠቀሜታ እንዳለው አንስተዋል።

የአደባባይ በዓላትን በጋራ ማክበራችን ከዚህም ባለፈ ለትብብር፣ ኢትዮጵያዊ አንድነትና አብሮነታችን መጠናከር ፅኑ መሰረት የሚያኖር መሆኑን ገልጸዋል።

የኢሬቻ በዓል ከምንም በላይ የወንድማማችነትና የፍቅር መገለጫ መሆኑን ተናግረው፤ ሁላችንም በሰላምና አብሮነት፤ በፍቅርና መተሳሰብ ልናከብረው ይገባል ብለዋል።

የከተማዋ ምክትል ከንቲባና የሥራ፣ ኢንተርፕራዝ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ፤ ኢትዮጵያ የካበተ ባህል፣ እሴትና ትውፊት ያላት አገር መሆኗን ገልጸዋል።

በመሆኑም የጋራ ሃብቶቻችንን ጠብቀን ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ ይኖርብናል ነው ያሉት።

በባዛሩ እና ኤግዚቢሽኑ ላይ ምርትና አገልግሎታቸውን ይዘው የቀረቡ አምራቾችና ነጋዴዎች በዝግጅቱ በርካታ ምርቶች የሚቀርቡ መሆኑን ተናግረዋል።

በባዛርና ኤግዚቢሽኑ በመሳተፋቸው ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅ እና የገበያ ትስስራቸውን ለማጠናከር የጎላ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።

የኢሬቻ በዓልን በማስመልከት የተከፈተው ባዛርና ኤግዚቢሽን በሁሉም ክፍለ ከተሞች ለሸማቾችና ጎብኝዎች ዝግጁ ሆኖ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም