ምሁራን የኢትዮጵያን እድገት የሚያሻሽሉና ሀገሪቱን ከተቀረው ዓለም ጋር የሚያስተሳስሩ ምርምሮች ላይ ትኩረት አድርገው መስራት ይጠበቅባቸዋል

152

መስከረም 18/2015/ኢዜአ/ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ምሁራን የኢትዮጵያን እድገት የሚያሻሽሉና ሀገሪቱን ከተቀረው ዓለም ጋር የሚያስተሳስሩ ምርምሮች ላይ ትኩረት አድርገው መስራት እንዳለባቸው አስገነዘቡ፡፡

21ኛው ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ጥናት ጉባኤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በጉባኤው ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሪሾ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃናን ጨምሮ ሌሎች ምሁራን፣ ተመራማሪዎችና እንግዶች እየተሳተፉ ነው።

ዛሬን ጨምሮ ለአራት ተከታታይ ቀናት የሚካሄደው ጉባኤ "'የኢትዮጵያ ጥናት ዓለም አቀፋዊ እና ብሔራዊ አውድ፣ተግዳሮትና ጽናት" በሚል ሚሪ ሐሳብ እየተካሔደ ይገኛል።

ፕሬዝደንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በዚሁ ወቅት በጥናትና ምርምር ስራዎች ላይ የሚካሄዱ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች የአገርን ልማት በጥናት ላይ የተመሰረተ ለማድረግ ጉልህ ጠቀሜታ ይኖራቸዋል ብለዋል።

ምሁራን ይህን እድል በመጠቀምም የኢትዮጵያን እድገት በሚያሻሽሉ ጉዳዮች ላይ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ምን ደረጃ ላይ እንዳለች በቅጡ በመገንዘብም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና የእውቀት ፍላጎትን ለማስፋት በጥናት ላይ የተመሰረቱ ተግባራት ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና፤ ዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያን ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ለማሻሻል በሚደረጉ ስራዎች ሁሉ የራሱን የጥናትና ምርምር አሻራ እያሳረፈ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ተወዳዳሪነት ለማሳደግም አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን ያገናዘቡ የጥናት  ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በቀረጸው የ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ መሰረትም ቅድሚያ በተሰጣቸው የልማት ግቦች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የአፍሪካን የ2063 ዘላቂ ልማት አጀንዳን ባገናዘበ መልኩ ዩኒቨርሲቲውን አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተዋዳዳሪነት ለማሳደግ በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑንም እንዲሁ፡፡

የኢትዮጵያ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ታከለ መርዕድ፤ በጉባኤው ላይ በ31 የፓናል ውይይቶች ከ275 በላይ ጥናታዊ ጹህፎች ይቀርባሉ ብለዋል።

በፓናል ውይይቱም ከ40 አገራት የተወጣጡ 75 ዓለም አቀፍ ምሁራንን ጨምሮ ከ21 የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ ተመራማሪዎች እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል።

በጉባኤው  በኢትዮጵያ የተካሄዱ ጥናቶችን በሚመለከት በተለያዩ ምሁራን የተዘጋጁ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ምክክር ከተደረገ በኋላ የቀጣይ ምልከታ ይቀመጣል ተብሎ ይጠበቃል።

20ኛው የኢትዮጵያ ጥናት ጉባኤ ከአራት ዓመታት በፊት 2011 ዓ.ም በመቐሌ ዩኒቨርሲቲ መካሄዱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም