አሲዳማ አፈር ለማከም እንዲረዳ ከ1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ኖራ ለአርሶ አደሩ ይከፋፈላል - ሚኒስቴሩ - ኢዜአ አማርኛ
አሲዳማ አፈር ለማከም እንዲረዳ ከ1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ኖራ ለአርሶ አደሩ ይከፋፈላል - ሚኒስቴሩ
አዳማ መስከረም 18/2015(ኢዜአ)… በዘንድሮ ዓመት አሲዳማ አፈር ለማከም እንዲረዳ ከ1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ኖራ ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት እየሰራ እንደሚገኝ የግብርና ሚኒስቴር ገለፀ።
በሚኒስቴሩ የግብዓት አቅርቦት መሪ የስራ አስፈፃሚ አቶ መንግስቱ ተስፋ ለኢዜአ እንደገለጹት ክልሎች ኖራ ለምርትና ምርታማነት እድገት መሰረት መሆኑን በመገንዘብ ከፌዴራል መንግስት ከሚደረግላቸው ድጋፍ በተጨማሪ ለኖራ ግዥ በጀት እንዲመድቡ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በአፈር አሲዳማነት የተጠቃውን የእርሻ ማሳ ለማከም የክልሎች የኖራ ፍላጎትና የሚለማውን ማሳ መጠን ለማወቅም የዳሰሳ ጥናት መካሄዱን ገልጸዋል።
በዚህም በዘንድሮ ዓመት 30 ሺህ ሄክታር የሚሆነውን በከባድ የአፈር አሲዳማነት የተጠቃውን መሬት ለማከም 1 ሚሊዮን ኩንታል ኖራ ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
የመንግስት ኖራ አምራች ፋብሪካዎች "በሙሉ አቅማቸው እየሰሩ እንዳልሆነ በጥናት ለይተናል" ያሉት መሪ ስራ አስፈፃሚው፤ ፋብሪካዎቹ በሙሉ አቅም እንዲያመርቱ ከማድረግ ባለፈ የሲምንቶ ፋብሪካዎችና የግሉ ሰክቴርም በኖራ ምርት በስፋት እንዲሰማራ እየሰራን ነው ብለዋል።
አርሶ አደሩ ዘንድ ያለውን የግንዛቤ እጥረት ለመፍታትም በተለይ በሰርቶ ማሳያ ጭምር የኖራ አጠቃቀምና የሚገኘውን ውጤት አርሶ አደሩ በተግባር ማሳ ላይ እንዲማር በየደረጃው ባሉ ባለድርሻ አካላት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
አርሶ አደሩ ኖራን በብድርና እጅ በእጅ ሽያጭ በመሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበራት ዘንድ እንዲያገኝ ከዩኒየኖች ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ መንግስቱ፤ ለዚህም የኖራ አቅርቦት ስርጭት መመሪያ መዘጋጀቱንም አመልክተዋል።
በክልሉ አጠቃላይ እየታረሰ ካለው 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር ማሳ ውስጥ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር የሚሆነው በከባድ አሲዳማነት መጠቃቱን የገለጹት ደግሞ በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የግብርና ግብዓትና ገጠር ፋይናንስ ዳይሬክተር ወይዘሮ ሙሽራ ሲሳይ ናቸው።
በተያዘው በጀት ዓመት 12ሺህ 500 ሄክታር አሲዳማ መሬት በኖራ ለማከም አቅደው እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም 250 ሺህ ኩንታል ኖራ ለማቅረብ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ የኖራ አቅርቦት የተሻለ እንዲሆን በኖራ ምርት የግሉን ሴክተር ተሳትፎ የማጠናከር ስራ እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው ባለፈው ዓመት ከ5ሺህ ኩንታል በላይ ኖራ በግሉ ሴክተር ለአርሶ አደሩ ተደራሽ መሆኑንም አክለዋል።
በደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ የአፈር ለምነት ማሻሻያ ዳይሬክተር አቶ ይሳቅ ዲያ በበኩላቸው በክልሉ እየታረሰ ካለው 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 43 በመቶ የሚሆነው በአፈር አሲዳማነት መጠቃቱን ጠቅሰዋል።
በተለይ 540 ሺህ 890 ሄክታር መሬት በከባድ የአፈር አሲዳማነት የተጠቃ በመሆኑ በልዩ ትኩረት ርብርብ የሚያስፈልግ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ትልቁ ማነቆ እየሆነ ያለው የኖራ አቅርቦት በሚፈለገው ደረጃ ያለመሆኑን ተናግረዋል።
በዘንድሮ ዓመት 2ሺህ 700 ሄክታር ማሳ በኖራ ለማከም እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም 43ሺህ ኩንታል ኖራ ለማቅረብ አቅድን ርብርብ እያደረግን ነው ብለዋል።
በአዳማ ከተማ የግሉን ሴክተር ያማከለ የግብርና ኖራ አቅርቦትና ስርጭት ሀገር አቀፍ የልምድ ልውውጥ መድረክ አሁንም በመካሄድ ላይ ይገኛል።