ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ሶማሊያ በሁለትዮሽና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ተስማሙ

መስከረም 18/2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያና ሶማሊያ በሁለትዮሽና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ተስማሙ፡፡

የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡

የሁለቱ አገራት መሪዎች በሁለትዮሸና ቀጠናዊና የትብብር ግንኙነት በሚጠናከርባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር አድርገዋል፡፡

የመሪዎቹን ውይይት የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ፤  ኢትዮጵያና ሶማሊያ ረዥም ዘመናትን የተሻገረና በህዝብ ለህዝብ ትስስር ጭምር የተጠናከረ ወዳጅነት አላቸው፡፡

በውይይታቸውም የሁለቱ አገሮች ወዳጅነት ይበልጥ በሚጠናከርባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውን ነው የተናገሩት፡፡

በሶማሊያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ መስዋትነት በመክፈል ጭምር ለሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ ሚና እያበረከተ መሆኑን አንስተው፤ በዚህም ፕሬዝዳንት  ሐሰን ሼክ መሐሙድ ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ምስጋና ማቅረባቸውን ገልጸዋል።  

የሁለቱ አገራት ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር እንደሚሰሩ ማረጋገጣቸውንም ነው አምባሳደር ተስፋዬ የተናገሩት፡፡

መሪዎቹ በውይይታቸው ኢትዮጵያና ሶማሊያ በሰላምና ደህንነት ከሚያደርጉት ትብብር ባሻገር በፖለቲካና በኢኮኖሚ እንዲሁም በቀጠናው ሰላም በትብብር ለመስራት ተስማምተዋል ነው ያሉት፡፡

በተለይም የአፍሪካ ቀንድ የተረጋጋ እንዲሆን አብሮ መሥራት እንደሚያስፈልግም አጽኖት ሰጥተው ተወያይተዋል ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሪታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም፤ መሪዎቹ በውይይታቸው ሁለቱ አገሮች በሰላምና ደህንነት ያላቸውን ጠንካራ ትብብር በኢኮኖሚው መስክም ማስፋት በሚችሉበት ጉዳይ ላይ መወያየታቸውን ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር ኢትዮጵያ በቁርጠኝነት እንደምትሰራ መግለጻቸውንም ነው የጠቆሙት፡፡

ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ በግንቦት 2014 ዓ.ም በተካሄደው የሶማሊያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አሸናፊ መሆናቸው ተከትሎ በሰኔ ወር ላይ በተከናወነው የፕሬዝዳንቱ በዓለ ሲመት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አሕመድ ተገኝተው መልእክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸውም የኢትዮጵያን ሰላምና ልማት ከጎረቤቶቻችን ለይተን የማናየው በመሆኑ ለቀጣናዊ ትስስር መጠናከር ከቀንዱ አገራት ጋር በትብብር እንሰራለን ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

ከዚህ አኳያ የኢትዮ-ሶማሊያ ግንኙነት እንዲጠናከር ኢትዮጵያ በቁርጠኝነት እንደምትሰራ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ መግለጻቸው ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም