ቀጥታ፡

በተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች እና ጅቡቲ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለወቅታዊ ሀገራዊ ጥሪ 576 ሺህ 681 ዶላር ተሰበሰበ

መስከረም 18 ቀን 2015 (ኢዜአ)በተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች እና በጅቡቲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለወቅታዊ ሀገራዊ ጥሪ 576 ሺህ 681 ዶላር ተሰበሰበ።

በዚህም መሰረት በተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ከ560 ሺህ ዶላር በላይ እንዲሁም በጅቡቲ ከ8 ሺህ 160 ዶላር በላይ ተሰብስቧል።

ድጋፉ የተሰበሰበው በተባበሩት አረብ ኤመሬቶች አቡዳቢ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ኮሚዩኒቲ ማሕበር፣ ከኩፖን ሽያጭ፣ ከሚስዮኑ ዲፕሎማቶችና ሠራተኞች መሆኑም ተነግሯል።

ድጋፉ በአቡዳቢ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ማሕበር 274 ሺህ ዶላር፣ ከኩፖን ሽያጭ 274 ሺህ ዶላር፣ ከሚስዮኑ ዲፕሎማቶችና ሠራተኞች ከደመወዝ መዋጮ 20 ሺህ 567 ዶላር በድምሩ 568 ሺህ 512.00 ዶላር መሰብሰቡን ከሚሲዮኑ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።

በዱባይ የኢትዮጵያውያን ኮሚዩኒቲ ማሕበርም የበኩሉን ድጋፍ ለማድረግ በዝግጅት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ የኢፌዴሪ ሚሲዮኖችም በተመሳሳይ ሁኔታ ሀብት በማሰባሰብ ላይ እንዳሉ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት መረጃ ይጠቁማል።

በተጨማሪም በጅቡቲ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ማህበርም እንዲሁ የ8 ሺህ 169 ዶላር አሰባስቦ አስረክቧል።ከማህበሩ አባላት የተሰበሰበውን ድጋፍ በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ የተረከቡ ሲሆን ድጋፉን ላደረጉ ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ ባስተላለፉት መልዕክት የማህበሩ አመራሮችና አባላት ያደረጉት ድጋፍ ለሌሎችም አርአያ የሚሆን ነው ብለዋል።

ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም በጅቡቲ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ማህበር አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም