ለአገር ዘላቂ ሰላም እና ልማት መረጋገጥ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን የሚወጣበት ወቅት ነው- ብፁዕ አቡነ መቃሪዮስ

92

ጅግጅጋ መሰከረም 17/2014 (ኢዜአ) ለአገር ዘላቂ ሰላም እና ልማት መረጋገጥ ሁሉም ዜጋ ከመቼውም ጊዜ በላይ የድርሻውን የሚወጣበት ወቅት ነው ሲሉ የሶማሌ ክልል እና የምስራቅ ሐረርጌ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ መቃሪዮስ አስገነዘቡ።

የደመራ እና የመስቀል በአል በሰላም እንዲከበር ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ያከናወኑትን የተቀናጀ ተግባር በልማት እና በዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ ተግባራት እንደሚደግሙት ወጣቶች ተናግረዋል ።

የደመራ እና የመስቀል በአል በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች በደመቀ ስነስርአት ተከብሯል።

የሶማሌ ክልል እና የምስራቅ ሐረርጌ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መቃሪዮስ ባስተላለፉት መልዕክት ለአገር መረጋጋትና ዘላቂ ሰላም መስፈን ሁሉም ልዩ ስፍራ ሰጥቶ በመስራት ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ለማሻገር  መትጋት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በተለይም በሶማሌ  ክልል ለውጡን ተከትሎ የሚስተዋለው ሰላም እና የልማት እንቅስቃሴዎችን ለማጠናከር ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባ አመልክተዋል ።

ኢትዮጵያ ከገጠማት ችግር ተላቃ ትንሳኤዋ  ዕውን እንዲሆን ሁላችንም ለሰላም እና ለልማት ልዩ ትኩረት ሰጥተን መንቀሳቀስ ይኖርብናል” ሲሉ  ብፁዕ አቡነ መቃሪዮስ  አስታውቀዋል። ።

በአሉ በአገርና  በመላው አለም ለሚገኙ የእምነቱ ተከታዮች  የደስታ እና የአንድነት እንዲሆን ምኞታቸውን አስተላፈው ለበአሉ ማማርና መድመቅ  አስተዋጾ ላበረከቱ ምስጋና አቅርበዋል ።

የሶማሌ ክልል አገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ መላዕከ መዊዕ ቆሞስ አባ ፅጌ ደስታ በበኩላቸው ለመላው የእምነቱ ተከታዮች በአሉ  የፍቅር ፣ የሰላም እና የአንድነት እንዲሆን ተመኝተዋል።

“በተለይ ወጣቶች ከፀጥታው አካል ጋር ተቀናጅተው የጀመሩት የሰላም ማረጋገጥ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል” ብለዋል።

በበአሉ ላይ የተሳተፉ ወጣቶች ያለሰላም  ምንም ነገር መፈፀም እንደማይቻል ተናግረው “ሰላም የሁሉም እንቅስቃሴዎች መሠረት በመሆኑ ለሰላም መከበር ተሳትፏችን ተጠናክሮ ይቀጥላል “ ብለዋል።

ከወጣቶቹ መካከል ቴዎድሮስ አበበ ለአካባቢ ፣ለአገር ዘላቂ ሰላም እና ልማት መረጋገጥ ወጣቶች የጀመሩትን የተቀናጀ ጥረት እንደሚያጠናክሩ ተናግሯል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም