ቀጥታ፡

ወጣቶች ሀገር ፀንታ እንድትቀጥል ትውልዳዊ አደራቸውን ሊወጡ ይገባል- ሊቀ-ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዩሃንስ

ጎንደር መስከረም 17/2015 (ኢዜአ) -ወጣቶች የመስቀሉን የፍቅርና የአንድነት አስተምህሮ በመገንዘብ ሀገር ፀንታ እንድትቀጥል ትውልዳዊ አደራቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የሰሜን ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ-ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዩሃንስ አሳሰቡ፡፡

በጎንደር ከተማ የመስቀል ደመራ በዓል በከተማው መስቀል አደባባይ በርካታ የእምነቱ ተከታዮችና ቱሪስቶች በተገኙበት ዛሬ በታላቅ ሃማኖታዊ ስርዓት ተከብሯል፡፡

ብፁዕ አቡነ ዩሃንስ በበአሉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ወጣቱ የኢትዮጵያን አንድነትና ክብር በማስጠበቅ ጸንታ አንድትቀጥል የአባቶቹን ታሪክና ገድል ሊከተል ይገባል ብለዋል፡፡

"ሀገር ጸንታ የኖረችው በየዘመናቱ በነበሩ ወጣቶች የትውልድ ቅብብሎሽ ነው" ያሉት ብጹዕ አቡነ ዮሃንስ ወጣቱ ለሃይማኖቱና ለሀገሩ ቀናኢ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

የእምነቱ ተከታዮች በአሉን ስናከብር በጦርነቱ የተጎዱና የተፈናቀሉ ወገኖችን በማሰብና በመርዳት ጭምር ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

"ከ300 ዓመት በላይ ተቀብሮ የቆየውን መስቀል በንግስት እሌኒ አማካኝነት ከተቀበረበት እንዲወጣ ማድረጉ የመስቀሉን ሃያልነትና ከፍታ የሚያመላክት ነው" ብለዋል።፡፡

"በአሉን ስናከብር አሁን ያለውን የከተማችን ሰላም አስተማማኝና ዘላቂ በማድረግ ነው" ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ ናቸው፡፡

"የመስቀል በዓል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት በማይዳሰሱ የሰው ልጆች ሁሉ ወካይ ቅርስ ሆኖ የተመዘገበ ድንቅና ብርቅ የሆነ የዓለም ሀብት ነው" ብለዋል፡፡

"ይህን ድንቅ መንፈሳዊ ቅርሳችንን የበለጠ የምናደምቀው አንድነታችንን በማጠናከር፣ በመረዳዳት፣ በመተሳሰብና በመዋደድ ጭምር ሊሆን ይገባል" ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የህወሓት የሽብር ቡድን ለ3ኛ ጊዜ የከፈተውን ጦርነት በመመከት ረገድ የከተማው ህዝብ እያደረገ ያለውን አኩሪ የደጀንነት ተሳትፎ  አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

"የመሰቅል በዓል በጎንደር ከተማ ሃይማኖታዊ ስርዓቱንና ባህላዊ ትውፊቱን በጠበቀ መንገድ መከበሩ የከተማው ህዝብ አንድነትና ፍቅር ማሳያ ነው" ያሉት ደግሞ በበአሉ የታደሙት የከተማው ነዋሪ አቶ መልካሙ መሳፍንት ናቸው፡፡

ወጣት ባምላኩ ፈንታሁን በበኩሉ "የኢትዮጵያ ጠላቶች የሰላም አማራጮችን በመዝጋት ጦርነት ቢከፍቱም እኛ ወጣቶች ከመከላከያ ጎን በመሰለፍና ለሀገራችን ዘብ በመቆም በዓሉን በሰላም ለማክበር በቅተናል" ሲል ገልጿል።

በዓሉ ደመራ በመለኮስና ሃይማኖታዊ ዝማሬዎች በማቅረብ በሰላም ተከብሮ ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም