የመስቀል ደመራ በዓል በመላው ዓለም የሚገኙ ዜጎች ሊታደሙበትና ሊጎበኙት የሚገባ ቅርስ ነው -የውጭ አገራት ጎብኚዎች

94

መስከረም 17/2015/ኢዜአ/ የመስቀል ደመራ በዓልን በመላው ዓለም የሚገኙ ዜጎች ሊታደሙበትና ሊጎበኙት የሚገባ ቅርስ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የውጭ አገራት ጎብኚዎች ገለጹ።

በኢትዮጵያ በየዓመቱ የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል ከጊዜ ወደ ጊዜ የጎብኚዎችን ቀልብ እየሳበ ነው።     

ደመራ በሚለኮስበት ቦታ ያለው ሃይማኖታዊ ስነ-ስርዓት፣ ወረቡ እና ከተለያዩ አድባራት የተውጣጡ ሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ዝማሬ ልዩ ገጽታ ያለው ነው።  

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በዓለም ከማይዳሰሱ ቅርስነት የተመዘገበው የመስቀል ደመራ በዓል የአገሪቷን ገጽታ በመቀየር ረገድም ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑም እሙን ነው።

በትላንትናው ዕለትም የደመራ በዓል በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች እና የኃይማኖት አባቶች በተገኙበት ተከብሯል።  

ኢዜአ ያነጋገራቸው የበዓሉ ታዳሚዎች በሰጡት አስተያየት ባዩት ነገር ደስተኞች መሆናቸውን ገልጸው የመስቀል ደመራ በዓል ዓለም ሊጎበኘው የሚገባ ትልቅ ቅርስ ነው ብለዋል።       

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ከእንግሊዝ ኦክስፎርድ የመጡት ክሪሲዳ ማርከስ "እውነተኛው መስቀል የተገኘበትን ቀን ለማክበር እዚህ በመገኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ" ሲሉ ተናግረዋል። 

ክሪሲዳ ማርከስ ከዚህ በፊትም በጎንደር ከተማ የደመራ በዓል መታደማቸውን አስታውሰው በዓሉ ልዩ እና መላው ዓለም ሊጎበኘው የሚገባ ቅርስ ነው ብለዋል።       

ሌላዋ ጎብኚ ክሪስቲን ቻሎት በበኩላቸው ከስዊዘርላንድ ጄኔቫ መምጣታቸውን ገልጸው የግሪክ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ መሆናቸውን አንስተዋል።  

በእኛ እምነትም ንግስት እሌኒ መስቀሉን ያገኘችበት በዓል ይከበራል፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አከባበር ግን ለየት ያለ ገጽታ አለው ብለዋል።   

ብዛት ያለው ህዝብ በአንድ ቦታ፣ ነጭ ልብስ ለብሶ፣ በአንድ ላይ ዝማሬዎችን ሲያሰማ ማየት የተለየ ስሜትን የሚፈጥር ሁነት ነው ሲሉም ተናግረዋል።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም