የደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ክላስተር ምክር ቤት ተመሰረተ

22

ጅማ፣ መስከረም 17/2015(ኢዜአ)-- የግብርና ዘርፉን በተሻለ መልኩ መደገፍ ያስችላል የተባለው የደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ክላስተር ምክር ቤት ተመሰረተ።

በኦሮሚያ ክልል የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመንና ምርታማነትን ለመጨመር የዘርፉ ተቋማት በትብብር መስራት እንደሚገባቸው ተገልጿል።

ለዚህም ሲባል በጅማ ከተማ የግብርናውን ዘርፍ የበለጠ ይደግፋል የተባለው የደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ክላስተር ምክር ቤት ተመሰረቷል።

ምክር ቤቱ የጅማ፣ የቡኖ በደሌና የኢሉባቦር ዞኖችን የሚያቅፍ ሲሆን የግብርናውን ዘርፍ በተሻለ መልኩ ለመምራት እንደሚረዳም ታውቋል።

ምክር ቤቱ ለቀጣይ ሁለት አመታት በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሚመራ ሲሆን የምክር ቤቱ ሰብሳቢም የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕረዚዳንት ዶክተር ጀማል አባ ፊጣ እንደሆኑ ተነግሯል።

ዶክተር ጀማል የምክር ቤቱን መመስረት ዋና አላማ አስመልክተው እንደተናገሩት ከዚህ በፊት የግብርናው ዘርፍ ያልተቀናጀና የተበታተነ እንደነበር ገልፀው ስራዎችን ወጥነት ባለው መንገድ ለማከናወን ታስቦ የተመሰረተ መሆኑን ተናግረዋል።

በኦሮሚያ ክልል በ7 ክላስተሮች ከተመሰረቱት ምክር ቤቶች አንዱ የደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ መሆኑን የገለጹት ሰብሳቢው ምክር ቤቱ ዘርፋን ለማዘመን የሚያግዙ ጉዳዮች ላይ ይመክራል፣ ያስተባብራል፣ ችግሮችን በመለየት መፍትሄ እንዲያገኙ ያደርጋል ብለዋል።

የግብርና ምርምር ተቋማት፣ የዞንና የወረዳ የግብርና ጽህፈት ቤቶች እንዲሁም በአካባቢው የሚገኙ በፌዴራልም ሆነ በክልል የሚመሩ የግብርና አካላት ጋር በትብብር የዘርፋን ችግሮች ለመፍታት የሚተጋ መሆኑን ዶክተር ጀማል ተናግረዋል።

የኦሮሚያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ቢሮ አስተባባሪ ዶክተር ሳሙኤል ቱፋ በበኩላቸው በክልሉ በሰባት ክላስተር የተዋቀሩ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት መመስረታቸውን አስታውሰው አላማውም የክልሉን ግብርና የበለጠ ማሳደግ ነው ብለዋል።

ምክር ቤቱ በክልሉ የሚገኙ የግብርና ዘርፍ ተዋናይ የሆኑ ተቋማትና ባለሞያዎችን በማስተባበር ለዘርፋ እድገት ማነቆ የሆኑ ችግሮችን በመለየት መፍትሔ መስጠት ላይ ያተኩራል ብለዋል።

በተለይም በግብርና ዘርፍ የትኛው ተቋም ምን ይስራ የሚለውን በተገቢው መንገድ ለመከታተልና በአምራቹ ህብረተሰብ የሚነሱ የግብአት አቅርቦት እጥረትና የተደራሽነት ውስንነትን ለመቅረፍ ያግዛል ብለዋል።

በግብርና ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ምስረታው የግብርና ምርምር ተቋማት ተወካዮች፣ የዩኒቨርስቲ ሙሁራን እና ከሶስቱም ዞኖች የተውጣጡ የግብርና ዘርፍ ተዋናዮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም