በሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የተገነቡና የታደሱ የአቅመ ደካማ ቤቶች ርክክብ ተደረገ

71

ሻሸመኔ መስከረም 17/2015/ ኢዜአ/--በሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት እድሳትና እንደ አዲስ ግንባታ የተደረገላቸው የአቅመ ደካማ ቤቶች ርክክብ ተደርጓል።

ከተማ አስተዳደሩ በክረምት በጎፈቃድ አገልግሎት ያስገነባውንና ያሳደሰውን 79 ቤቶችን ነው ለአረጋዊያን እና ለአቅመ ደካሞች ያስረከበው።

የቤቶቹ እድሳትና ግንባታ የተደረገው በወጣቶች፣ በባለሃብቶች እንዲሁም በሌሎች በጎ አድራጎት ማህበራት አማካኝነት መሆኑም ታውቋል።

ቤታቸው የታደሰላቸው አቅመ ደካማ አረጋውያን እድሳቱ ይደርስባቸው የነበረውን  ችግር የቀረፈላቸው መሆኑንና ተግባሩም የሚያስመስገን ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር  ሴቶች እና ህፃናት ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ገነት ገብረአምላክ በበኩላቸው አረጋዊያንና ችግረኛ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን መርዳት ከሁሉም የሚጠበቅ ተግባር ነው ብለዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ካሁን በፊት ለአረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች የተለያዩ ስብዓዊ ድጋፎችን እያደረገ መቆየቱን አስታውሰው አሁን ደግሞ በበጎ ፈቃድ አማካኝነት 37 ቤቶች በአዲስ መልክ መገንባት እና 42 ቤቶች ደግሞ እድሳት መደረጉን ገልጸዋል።

በበጎ ፈቃድ መልክ ወጪ የተደረገው ገንዘብም ከ10 ሚሊዬን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ከተማ አስተዳደሩ በጎ አድራጊዎችን በማስተባበር 3 ሺህ 500 ለአቅም ደካማ ቤተሰብ ተማሪዎች 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም