የመስቀል ደመራ በዓል በጎንደር ከተማ በደማቅ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ስርአት እየተከበረ ነው

ጎንደር መስከረም 17/2015 (ኢዜአ) በጎንደር ከተማ የመስቀል ደመራ በዓል በታላቅ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ስርአት በዛሬው እለት በድምቀት እየተከበረ ነው።

በከተማው መስቀል አደባባይ እየተከበረ በሚገኘው የደመራ በዓል ላይ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የጎንደር ከተማና አካባቢው የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ታድመዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሊቀ-ጳጳስ አቡነ ዮሐንስ፣ የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ እንዲሁም የከተማውና የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች በበዓሉ ላይ ተሳትፈዋል።

May be an image of 5 people

ደመራው እስኪለኮስ ድረስ ስለበዓሉ ታሪካዊ አመጣጥ፣ ስለመስቀሉ ክብርና ሌሎች ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎች ይከናወናሉ።

በአሁኑ ወቅትም በዓሉን ለማድመቅ ካህናትና የሰንበት ተማሪዎች የተለያዩ ያሬዳዊ ዜማና ቅኔ እንዲሁም መዝሙሮችን እያቀረቡ ሲሆን በበዓሉ የታደመውም ህብረተሰብ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ክዋኔዎችን በማቅረብ ለበዓሉ ድምቀት ሰጥቷል።

የወጣው መርሃግብር እንደሚያሳየው በዓሉን አቅመ ደካሞችንና የተፈናቀሉ ወገኖችን በመርዳትና በመደገፍ በአብሮነት ማክበር እንደሚገባ በሃይማኖት አባቶች መልዕክት ያስተላልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በጎንደር ደመራ የሚደመረው ከመስቀል በዓል አንድ ቀን ቀደም ብሎ ሲሆን ደመራው የሚለኮሰው ደግሞ በመስቀል በዓል ከቀኑ 7:00 ሰዓት አካባቢ ነው።

የበዓሉ ተሳታፊዎች ትናንት ምሽት የተደመረውን ደመራ ዛሬ ከለኮሱ በኋላ በዓሉ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ መርሃ ግብሩ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም