ቀጥታ፡

የመስቀል በዓል አሸናፊነት የሚገኘው በጉልበት ሳይሆን በፍቅር እንደሆነ ማሳያ ነው--ብፁዕ አቡነ አብርሃም

ባህር ዳር መስከረም 17/2015(ኢዜአ)-- "የመስቀል በዓል አሸናፊነት የሚገኘው በጉልበት ሳይሆን በፍቅር መሆኑን ያረጋገጠ ታሪካዊ እለት ነው" ሲሉ የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ አብርሃም ገለጹ።

የደመራ በዓል ሃይማኖታዊና ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ በርካታ ምዕመን በተገኘበት በባህር ዳር ከተማ በድምቀት ተከብሯል።

ብፁዕ አቡነ አብርሃም በበዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት "ሁሉን የፈጠረና ሁሉን የሚገዛ አምላክ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ መሞቱ ጉልበት አጥቶ ሳይሆን ማሸነፍ የሚቻለው በፍቅር መሆኑን ለማሳየት ነው" ብለዋል።

"በኋላም ሞትን በትንሳኤ ድል በመንሳት ሃያልነቱን አስመስክሯል" ያሉት አቡነ አብርሃም፣ ህዝበ ክርስቲያኑ የመስቀል በዓልን ሲያከብር በዓሉ ፍቅርና አንድነት የነገሰበት፤ ጥላቻ የተወገደበት መሆኑን መገንዘብ ጭምር መሆን እንዳለበት አመልክተዋል።

"የመስቀሉ ታሪክ አሸናፊነት የሚገኘው ጉልበት ስላለ ብቻ ሳይሆን በፍቅርና በማስተዋል መሆኑን የሚያስተምረን ነው ሲሉም" አክለዋል።

ኢትዮጵያ ሁሉ ነገር የሞላባት ሀገር መሆኗን የገለጹት አቡነ አብርሀም፣ "ችግሮች ሁሉ ተወግደውና ስደት ቆሞ ሁሉም በሀገሩ እንዲኖር መገፋፋትንና ጥላቻን ማስወገድ ይገባል" ብለዋል።

"መስቀል በፈተናዎች ውስጥ ሆኖም ማሸነፍ እንደሚቻል ያየንበት የጽናት ተምሳሌት ነው" ያሉት ደግሞ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ ናቸው።

ፈተና ደካሞችን ተስፋ አስቆርጦ ከዓላማቸው ሲያስናክል፤ ለጠንካሮች ደግሞ እንደ ብረት ጸንተው ችግሮችን የሚያልፉበት መንገድ መሆኑን ተናግረዋል።

"ኢትዮጵያ አሁን በፈተና ውስጥ ብትገኝም የመስቀሉ ታሪክ የሚያሳየው ፈተናዎችና መሰናክሎች የሚታለፉበትን ስልት በመቀየስ ሀገር አሸናፊ መሆኗ የማይቀር መሆኑን ነው" ብለዋል።

አያይዘውም በባህር ዳር ከተማ አሁን ችግር ያለ ለማስመሰል የሚሰሩ አካላት እንዳሉ የጠቀሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው፣ "የደመራ በዓል ያለምንም ኮሽታ በሰላም መከበር ከተማዋ ፍጹም ሰላም ለመሆኗ  ትልቅ ማሳያ ነው" ብለዋል።

ዶክተር ድረስ የከተማዋ ወጣቶችና መላው ነዋሪ የሰላም ዘብ ሆነው ከተማዋን ለኑሮና ለቱሪስት የተመቸች ለማድረግ ግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆናቸው ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም