በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የመስቀል ደመራ በዓል በድምቀት እየተከበረ ነው

165

ባህር ዳር እና ደሴ (ኢዜአ) መስከረም 16/2015--በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የመስቀል ደመራ በዓል በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ሃይማኖታዊ ስርዓቱን በጠበቀ መንገድ በደመቀ ሁኔታ እየተከበረ ነው።

በዓሉ በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ሃይማኖታዊ ስርዓቱን በጠበቀ ሁኔታ የሃይማኖት አባቶችና በርካታ የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት እየተከበረ ነው።

በባህር ዳር ከተማ እየተከበረ ያለውን በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባህር ዳር ከተማ ሀገረ ስብከት ሊቀ-ጳጳስ ብፅዕ አቡነ አብርሃም በጸሎተ ቡራኬ አስጀምረውታል።

በበዓሉ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች፣ የየአድባራቱ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች እና ከፍተኛ ቀጥር ያላቸው የእምነቱ ተከታዮች በታደሙበት ነው በደማቅ ሁኔታ እየተከበረ ያለው።

በተመሳሳይ በደሴ ከተማ አስተዳደር የመስቀል ደመራ በዓል ሃይማኖታዊ ስርዓቱን ጠብቆ በሆጤ ስታድዮም በተለያዩ ሃማኖታዊ ስርአቶች በመከበር ላይ ነው።

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱ ሁሴን በእዚህ ወቅት እንዳሉት፣ በዓሉ ሲከበር በኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም እንዲመጣ ሁሉም ፈጣሪውን በመለመን ሊሆን ይገባል።

የመስቀል ደመራ በዓል ሲከበር የመከራ ዘመን አልፎ የሰላም ዘመን እንዲመጣ ንግስት እሌኒ ለዘመናት ተክብሮ የቆየውን መስቀል እንድታወጣ ፈጣሪ የሰጣትን ፀጋ በማሰብ ጭምር መሆን እንዳለብት አመልክተዋል።

"በዓሉ የትዕግስት፣ የመተማመን፣ የፍቅርና የፅናት ተምሳሌት በዓል ነው" ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፣ ሀገር ተረጋግታ አስተማማኝ ሰላምና ልማት ለማስፈን ሁሉም ፈጣሪውን መለመን እንዳለበት አመልክተዋል።

የሰላም፣ የአብሮነት፣ የመተሳሰብ፣ የመደጋገፍና የመከባበር እሴቶቻችንን አጠናክረን ኢትዮጵያን መጠበቅ የሁላችንም ሀላፊነት ነው ሲሉም አክለዋል።

በክልሉ የመስቀል ደመራ በዓል በደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር በንጉስ ተክለሃይመኖት አደባባይ፣ እንዲሁም በሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ ከተማም እየተከበረ ሲሆን ከሰዓታት በኋላም ደመራው ይለኮሳል ተብሎ ይጠበቃል።

ከእዚህ በተጨማሪ በጎንደር እና በሰቆጣ ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውሃ ከተማ የደመራ ችቦ የመለኮስ  ስነ ስርዓት በነገው እለት እንደሚካሄድ ታውቋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም