በዓሉ ሲከበር ለአንድነትና አብሮነት መጠናከር መሰረት የሆኑትን ይቅርታና ፍቅር በማጎልበት ሊሆን ይገባል--አቶ ደስታ ሌዳሞ

86

ሀዋሳ መስከረም 16 /2015  (ኢዜአ) "የመስቀል በዓልን ስናከብር ለአንድነትና አብሮነት መጠናከር መሰረት የሆኑትን ይቅርታና ፍቅርን በማጎልበት ሊሆን ይገባል" ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ለመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

አቶ ደስታ እንዳሉት የመስቀል በዓል አምላክ ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር ያሳየበትና ይቅርታ ያደረገበት ታላቅ መለኮታዊ አንድምታ አለው።

በዓሉ ፍቅር፣ ሰላም፣ ይቅርታና መተሳሰብ የሚንጸባረቅበት በመሆኑ፣ ሲከበር ከሌሎች ጋር አንድነትን በሚያጎለብት መልኩ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።

"ፈጣሪ ለሰው ልጆች የከፈለውን መስዋዕትነት በማሰብ ለእርስ በርስ ግንኙነት መጠናከር ወሳኝ የሆኑትን ፍቅር እና ይቅርታን እያጎለበትን በዓሉን ማክበር ይገባል" ሲሉም አቶ ደስታ አመልክተዋል።

"የመስቀል በዓል በዩኔስኮ ከተመዘገቡ የማይዳሰሱ ቅርሶቻችን አንዱ በመሆኑ የምንኮራበት ነው" ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በዓሉን ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ ከሁሉም እንደሚጠበቀ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የአሸባሪውን ህወሓት ሴራ ለማክሸፍ በተባበረ ክንድ የመከላከል ሥራ እየተሰራ ያለበትና ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው በአንድነት የሚከፍሉተን መስዋዕትነት በማጠናከር የጠላትን ሴራ ማክሸፍ እንዳለባቸው አመላክተዋል።

"የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስኬቶችን በማጠናከር ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ  በየተሰማራንበት ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን እንረባረብ" ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

የመስቀል በዓል ሲከበር ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ያለንን ክብርና አብሮነት በማሳየት መሆን እንዳለበተም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም