በኩባ አውሮፕላን ተከስክሶ ከ100 በላይ ሰዎች ሞቱ

561
ግንቦት 11/2010 በኩባ ሃቫና ጆሴ ማረቲ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ ቦይንግ 737-201 አውሮፕላን ተከስክሶ ከ100 በላይ ሰዎች ሞተዋል፡፡ ቢቢሲ የሀገሪቱን መገናኛ ብዙሃን ዋቢ አድርጎ እንዳስነበበው አውሮፕላኑ 3 የበረራ ቡድኑ አባላትን ጨምሮ 110 ሰዎችን አሳፍሮ ነበር፡፡ ከአደጋው ሶስት ሰዎች በህይወት ቢተርፉም የጤናቸው ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑም በዘገባው ተመልክቷል፡፡ አውሮፕላኑ ከሃቫና ተነስቶ በሀገሪቱ በስተምስራቅ አቅጣጫ ወደ ምትገኘው ሆልጉይን በመብረር ላይ ሳለ ነው ብዙም ሳይቆይ የተከሰከሰው፡፡ አውሮፕላኑ ሶስት ሜክሲኳውያን የበረራ ቡድን አባላትን ጨምሮ 5 የውጭ ዜጎችን ያሳፈረ ሲሆን ቀሪዎቹ የሀገሪቱ ተወላጆች መሆናቸውም ነው በዘገባው የተመለከተው፡፡ ኩባ ከ1980ዎቹ ወዲህ ይህን መሰሉን የከፋ የአውሮፕላን አደጋ ስታስተናግድ የመጀመሪያዋ ሲሆን አደጋውን ተከትሎም የሁለት ቀናት ብሔራዊ ሀዘን ታውጇል፡፡ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሚጉዌል ዲያዝ ካነል አደጋው የደረሰበትን ቦታ ከጎበኙ በኋላ የአደጋውን መንስዔ የሚያጣራ ብሔራዊ ኮሚሽን መቋቋሙን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም