በህገ-ወጥ የገንዘብ ማስተላለፍ ተግባር ላይ የተሰማሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት አስጠነቀቀ

418

መስከረም 16 ቀን 2015 (ኢዜአ) በህገ-ወጥ የገንዘብ ማስተላለፍ ተግባር ላይ የተሰማሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት አስጠነቀቀ፡፡

የፋይናንስ ወንጀሎችን የሚፈፅሙ አካላትን እና ግብረ-አበሮቻቸውን ከአገር ውስጥ ባለድርሻ አካላትና ከውጭ አገራት አጋር ተቋማት ጋር በመሆን በህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተገልጿል።

የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ለኢዜአ በላከው መግለጫ፤ በውጭ የሚኖሩ አንዳንድ አካላት ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ግብረ-አበሮቻቸው ጋር በመመሳጠርና ወደ ኢትዮጵያ የሚላከውን የውጭ ምንዛሬ በህገ-ወጥ መንገድ በማስተላለፍ የኢኮኖሚ አሻጥር እየፈጸሙ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ለአብነትም አድራሻቸውን በውጭ ሀገራት ያደረጉ እንደ "አዶሊስ"፣ "ሸጌ"፣ "ሰላም"፣ "ሬድ ሲ" የተሰኙ እና ሌሎች አካላት በተጠቀሰው ህገ-ወጥ ተግባር ተሰማርተው ይገኛሉ ነው ያለው፡፡

እነዚህ አካላት ሀሰተኛ ደረሰኝ አዘጋጅተው ወደ ኢትዮጵያ ባንኮች የሚልኩ በማስመሰል የውጭ ምንዛሬው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ እያደረጉ መሆኑንም የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎቱ ያስታወቀው፡፡

እነዚህ ህገ-ወጥ አካላት በኢትዮጵያ ካሉ ከ600 በላይ ግብረ-አበሮቻቸው ጋር በመተባበር እንደሚሰሩም ነው የገለጸው፡፡

እነዚህ አካላት ኢትዮጵያ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ በውጭ አገራት ከማስቀረት በተጨማሪ ወደ ኢትዮጵያ የሚላከውን ገንዘብ የኮንትሮባንድ ንግድን ጨምሮ የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች መፈፀሚያ እንዲውል እያደረጉ ነው፡፡

በመሆኑም የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ካሉ አጋር ተቋማት ጋር በመቀናጀት በተጠቀሰው ወንጀል የተሰማሩ አካላትን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አጽኖት ሰጥቶ ገልጿል፡፡

በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በወንጀሉ የሚሳተፉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡም አስጠንቅቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም