ቪታ ማካሮኒና ቪቫ ፓስታ አምራች ድርጅት ጊዜ ያለፈባቸውን ምርቶች ዳግም ሲያመርት በመገኘቱ ርምጃ ተወሰደበት - ኢዜአ አማርኛ
ቪታ ማካሮኒና ቪቫ ፓስታ አምራች ድርጅት ጊዜ ያለፈባቸውን ምርቶች ዳግም ሲያመርት በመገኘቱ ርምጃ ተወሰደበት
አዲስ አበባ መስከረም 10/2011 ለምለም ፉድ ኮምፕሌክስ አምራች ድርጅት የሚያመርታቸውን ቪታ ማካሮኒና ቪቫ ፓስታ ጊዜ ያለፈባቸውን ምርቶች ከጤናማ ምርቶች ጋር በማቀላቀል ሲያመርት በመገኘቱ እርምጃ መወሰዱን የኢትዮጵያ የምግብ፣ መድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ። የባለስልጣኑ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን አብርሃም ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ድርጅቱ ጊዜያቸው ባለፈባቸው የተበላሹ የማካሮኒና ፓስታ ምርቶችን ዳግም በመፍጨትና ከጤናማ ምርቶች በማቀላቀል ሲያመርት በመገኘቱ ፋብሪካው ምርት እንዲያቆምና ድርጅቱ እንዲታሸግ ተደርጓል። ድርጅቱ የሚያመርታቸው ቪታ ማካሮኒና ቪቫ ፓስታ ምርቶች ጊዜ ያለፈባቸውን ከጤናማው ጋር በመቀላቀል ሲያመርት በባለስልጣኑ ተደርሶበታል። ባለስልጣኑ ከወሰደው የፋብሪካ ማሸግ እርምጃ በተጨማሪ ድርጅቱን ለህግ የማቅረብ ስራ የሚሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። ምርቶቹ በገበያ ላይ የተሰራጩ በመሆናቸው ህብረተሰቡ ባለስልጣኑ አረጋግጦ ደህንነቱን እስኪያሳውቅ ድረስ ምርቶቹን እንዳይጠቀምም አሳስበዋል። ምርቶቹን ሲሸጥ የተገኘ ማንኛውም ቸርቻሪም ሆነ ድርጅት ሲገኝ በየአካባቢው ለሚገኝ ተቆጣጣሪ ወይም ጤና ቢሮ ህብረተሰቡ በባለስልጣኑ ነፃ የስልክ መስመር 8482 ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርቧል።