“ጊፋታ” ኢትዮጵያውያን በአአብሮነትና በአንድነት የመኖር የቆየ ልምዳቸው ጎልቶ የሚወጣበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
“ጊፋታ” ኢትዮጵያውያን በአአብሮነትና በአንድነት የመኖር የቆየ ልምዳቸው ጎልቶ የሚወጣበት ነው
ሶዶ መስከረም 15/2015 (ኢዜአ) የወላይታ የዘመን መለወጫ በአል “ጊፋታ” ኢትዮጵያውያን በፍቅር፣ በመተጋገዝና በመረዳዳት በአብሮነትና በአንድነት የመኖር የቆየ ልምዳቸው ጎልቶ የሚወጣበት ነው ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ-መስተዳደር ደስታ ሌዳሞ አስታወቁ።
የወላይታ የዘመን መለወጫ “ጊፋታ” በዓል በወላይታ ሶዶ ስታዲዮም ዛሬ ተከብሯል ።
በስነስርዓቱ ላይ የታደሙት የሲዳማ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ እንዳሉት ኢትዮጵያውያን በምንም ምክንያት የማይለወጥና ሊነቃነቅ የማይችል የጸና አንድነት ያላቸው ህዝቦች ናቸው።
“የውስጥና የውጪ ጠላቶቻቸን ለዘመናት በመካከላችን ልዩነት በመፍጠር ሊከፋፍሉንና ሊያዳክሙን ቢሞክሩም ልዩነታችንን አቻችለንና ተደጋግፈን በአንድነት መጽናታችን ምኞታቸውን ከንቱ አድርጎታል” ብለዋል።
የወላይታ ዘመን መለወጫ “ጊፋታ” መላውን ኢትዮጵያውያን ከተለያዩ አካባቢዎች በማሰባሰብ ኢትዮጵያዊነት ጎልቶ እንዲወጣ የሚያደርግ የአብሮነት መገለጫ በዓል መሆኑን ተናግረዋል።
ርዕሰ መስተዳደሩ አክለውም አሸባሪው ህወሀትና ዘዋሪዎቹ በሲዳማና ወላይታ ህዝብ መካከል ግጭት ለመፍጠር በማሰብ ሲያካሂዱ የነበረው ሴራ ሳይሳካ የቀረው ሁለቱ ህዝቦች አንድ በመሆን መመከት በመቻላቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
"በሲዳማና ወላይታ ህዝቦች መካከል ያለው ትስስር ዛሬ የተጀመረ አይደለም" ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ “እኛ ከተፈጠርን ጀምሮ ቡሉኮ ስንፈልግ ወላይታ፣ ምርጥ ሰንጋ ስንፈልግ ከወላይታ አንል ነበር” ሲሉ አመልክተዋል።
የሲዳማ ክልል የሰላም የአብሮነትና የጋራ ክልል እንደሆነ የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ “መላው የወላይታና የኢትዮጵያ ህዝብ እንዳሻው ሊመላለስበት፣ ሊሰራበትና ሊኖርበት ይችላል” ብለዋል።
የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ ለማ በበኩላቸው እንደተናገሩት የወላይታ ብሄር ያለውን እሴት አውጥቶ ለመጠቀም ባለፉት ስርዓቶች ተጸእኖ ሲደረግበት መቆየቱን አስታውሰዋል ።
"ይሁንና ክልሉ የብሄረሰቦች መብትን ያስከበረው ህገ መንግስት ከጸደቀበት ጊዜ አንስቶ ማንነቱን ማውጣት ችሏል" ብለዋል።
አሁን ላይ አሸባሪው ህወሀት ሀገር ለማፍረስ ለሶስተኛ ጊዜ የከፈተውን ጦርነት ለመመከት የመከላከያ ሰራዊቱ እያደረገ ያለውን ተጋድሎ ለማገዝ መላው የወላይታ ህዝብ እያደረገ ያለው ድጋፍ አሁንም አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
የወላይታ ዘመን መለወጫ በዓል “ጊፋታ” ማጠቃለያ ስነ-ስርዓት ዛሬ ምሽት በዳመራ ስነ-ስርዓት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።