ቀጥታ፡

ምዕመኑ የደመራ በዓልን ሲያከብር አንደነቱንና አብሮነቱን በሚያጠናክር መልኩ መሆን አለበት--ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል

መስከረም 15/2015 (ኢዜአ) ህዝበ ምዕመኑ የደመራ በዓልን ሲያከብር አንደነቱንና አብሮነቱን በሚያጠናክር መልኩ መሆን አለበት ሲሉ የጋምቤላ፣ የአሶሳ፣ የቄለም ወለጋ፣ የምዕራብ ወለጋና የደቡብ ሱዳን አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል አሳሰቡ።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሩፋኤል የመስቀል ደመራ በዓልን አስመልክተው ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት የመስቀል ደመራ በዓል የአብሮነት፣ የአንድነትና የፍቅር መገለጫ በዓል ነው ብለዋል።

መስቀሉ ጥላቻ የተገደለበትና ፍቅርና አንድነት የሰፈነበት በመሆኑ ምዕመኑ በዓሉን ሲያከበር አንደነቱንና አብሮነቱን በሚያጠናከር መልኩ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።

ክርስቶስ የሞተውና የተሰቀለው ለሁሉም ነው እናም ህዝበ ምዕመኑ በዓሉን ሲያከብር ከዘረኝነትና ከአካባቢያዊነት አስተሳሰብ በጸዳ መልኩ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።

በዓላት ፍቅር የገባቸው ሰዎች መሸሸጊያ እንጂ ጥላቻ ያላቸው ሰዎች መሸሸጊያ አይደለም ያሉት ሊቀ ጳዻሱ ምዕመኑ ወደ መስቀል ደመራ በዓል ሲመጣ ፍቅርና አብሮነትን በማጽናት ነው ብለዋል።

የመስቀል ደመራ በዓል ለመላው የኢትዮጵያ ምዕመናን የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የአበሮነት በዓል እንዲሆንም ብፀዕነታቸው ተመኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም