ኢትዮጵያ በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ ሆናም በአትሌቲክሱ ዘርፍ ያስመዘገበቸውን ድል ታሪክ አይረሳውም -- ፌዴሬሽኑ

191

ደሴ መስከረም 15/2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ ሆና በአትሌቲክሱ ዘርፍ ያስመዘገበቸውን ድል ታሪክ አይረሳውም ሲሉ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ አበባ ዮሴፍ ገለፁ፡፡

በኮሎምቢያ ካሊ በተካሄደው የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ወክላ ብር ላስገኘችው አትሌት ፂዮን አበበ የእውቅናና ምስጋና ፕሮግራም በደሴ ከተማ ተካሂዷል፡፡

የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ አበባ ዮሴፍ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በተለያዩ ችግሮችና ፈተናዎች ውስጥ ሆናም በአትሌቲክሱ ዘርፍ ያስመዘገበቸውን ድል ታሪክ አይረሳውም፡፡

"ጀግኖች ልጆቿ እንደ አባቶቻቸው አንድነታችውን ጠብቀው በትብብር ክብራችንና ባንዲራችንን ከፍ አድርገዋል" ያሉት ወይዘሮ አበባ፤ የኢትዮጵያን ታላቅነት በዓለም አስመስከረዋል ሲሉ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ ከአሜሪካና ጃማይካ በመቀጠል በ12 ሚዳሊያ በ3ተኛ ደረጃ ማጠናቀቋን አስታውሰው፤ የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከሎችን በመደገፍ በቀጣይ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በትኩረት እንሰራለን ብለዋል፡፡

የተንታ አትሌቲክስ ማስልጠኛ ማዕከል ሀገርን የሚወክሉ ስመ ጥር አትሌቶችን እያፈራ በመሆኑ ማዕከሉን በመደገፍና በማገዝ ብቁ አትሌቶችን እንዲያፈራ ይደረጋል ብለዋል።

በማዕከሉ ላሉ አትሌቶች ትጥቅና ሌሎች ቁሳቁሶችን በመደገፍ ምቹ ሁኔታ እንፈጥራለን ሲሉም አስታውቀዋል፡፡

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር መንገሻ አየነ በበኩላቸው ጀግኖች አትሌቶች ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ከፍ ያደረጉበት መንገድ "ተባብረን በአንድነት ከቆምን የማናልፈው ፈተና እንደሌለ ማሳያ ነው" ብለዋል።

ለዚህ ድል ደግሞ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የሚተዳደረው ተንታ አትሌቲክስ ማስልጠኛ ማዕከል የራሱን ድርሻ መወጣቱን ጠቁመው፤ ቀጣይ ማዕከሉን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡

አትሌት ፂዮን አበበ ባስመዘገበችው ውጤት ዩኒቨርሲቲው መኩራቱንና መደሰቱን ጠቁመው፤ ሌሎች አትሌቶችም በዓለም ውድድሮች እንዲሳተፉ ለማድረግ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል።

አትሌት ፂዮን አበበ በበኩሏ ውድድሩ ፈታኝ ቢሆንም ለዚህ ውጤት እንድበቃ ላገዙኝ አሰልጣኞቼ፣ ቤተሰቦቼና ወሎ ዩኒቨርሲቲ ትልቅ ምስጋና አለኝ ብላለች፡፡

''ባገኘሁት ድል ሳልኩራራ የኢትዮጵያን ክብር በዓለም ከፍ ለማድረግ ቀጣይ ሰዓቴን አሻሽዬ አንደኛ ለመውጣትና ወርቅ ለማምጣት አሰራለሁ'' ብላለች፡፡

በተንታ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል 51 ሰልጣኝ አትሌቶች ያሉ ሲሆን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በኢትዮጵያ በተደረጉ የተለያየ ውድድሮች 49 ሜዳሊያዎችን ማምጣታቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በእውቅናና ምስጋና ፕሮግራሙ የፌዴራል፣ የክልልና የዞን የስራ ሃላፊዎች የተገኙ ሲሆን ለአትሌቷ የ150 ሺህ ብር የቤት ቁሳቁስና በኮምቦልቻ ከተማ የቤት መስሪያ ቦታ ተበርክቶላታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም