ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት በኤሌክትሪክ ሃይል ላይ ያተኮር ትራንስፖርትን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው

14

ባህር ዳር መስከረም 15/2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት በኤሌክትሪክ ሃይል ላይ ያተኮር የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ገለፁ።

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በኤሌክትሪክ ላይ የተመሰረተና "ጤናማ ትራንስፖርትን ማበረታታት" በሚል መሪ ሃሳብ ምክክር እየተካሄደ ነው።

May be an image of 1 person, sitting, standing and indoor

ሚንስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በምክክር መድረኩ ላይ እንደገለፁት የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በዓለም ላይ ከፍተኛ የድርቅ፣ የጎርፍ መጥለቅለቅና ሌሎች ችግሮች እየተፈጠሩ ይገኛሉ።

የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ዘርፉ በነዳጅ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ የአየር ንብረት ለውጥ ከሚከሰትባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ ነው ብለዋል።

በአገራችንም ለዘመናት የዘለቀው የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ዘርፍ የነዳጅ ጥገኛ ሆኖ በመቆየቱ ለውጭ ምንዛሬና ለአየር ብክለት ችግር መዳረጉን ቀጥሏል ነው ያሉት።

ይሄን ችግር ለመፍታትም በኤሌክትሪክ የሚሰራ ተሽከርካሪ፣ የባቡርና ሌሎች የትራንስፖርት አገልግሎቶችን ለማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል።

እስካሁንም የአዲስ አበባ ቀላል ባቡርና ከአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርቶች በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መሆናቸውን በማሳያነት አቅርበዋል።

በቀጣይ 10 ዓመትም በኤሌክትሪክ የሚስሩ ተሽከርካሪዎችንና የህዝብ ትራንስፖርቶች ወደ አገልግሎት ለማስገባት የማበረታቻ ስርአት መዘርጋቱን አስረድተዋል።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲም በኤሌክትሪክ የሚሰራ የትራንስፖርት አገልግሎትን ለማስፋት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ካሪኩለም ቀርፆ የሰለጠነ የሰው ሃይል ለማፍራት እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ በመሆኑ ተገቢው ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

May be an image of 1 person and standing

የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚፈልገውን የሰለጠነና የበቃ የሰው ሃይል ለማቅረብ በጥናት ላይ ተመስርቶ እየሰራ ነው።

በዚህም አገራችን በኤሌክትሪክ የሚሰራ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማስፋፋት የምታደርገውን እንቅስቃሴ ለማገዝ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይል ለማፍራት ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከውጭ አገራትና ከውስጥ ድርጅቶችና ተቋማት ጋር በትብብር የመስራት ልምድ አለው ያሉት ዶክትር ፍሬው፤ ፕሮግራሙን ውጤታማ ለማድረግም ከሚኒስቴሩ ጋር በቅርበት እንደሚሰራ ገልፀዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ አትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴን ጨምሮ ሌሎች የኤሌክትሪክ መኪኖች የሚገጣጥሙ ድርጅቶች ያላቸው ባለሃብቶች፣ ምሁራንና የፌዴራል የስራ ሀላፊዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም