በዓሉ ኢትዮጵያዊነት ጎልቶ የታየበት ነው--ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን

አሶሳ መስከረም15/2015 (ኢዜአ)- 35ኛው አገር አቀፍ የቱሪዝም ቀን በዓል ኢትዮጵየዊነትን አጉልቶ ባሳየ መልኩ መከበሩን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን አስታወቁ።

በአገር አቀፍ ደረጃ ለሶስት ቀን በአሶሳ ከተማ የተከበረው የቱሪዝም ቀን በዓል ዛሬ ተጠናቋል።

ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን በወቅቱ እንዳሉት በዓሉ ኢትዮጵያዊ አንድነት የጎላበት መድረክ ሆኖ ተጠናቋል።

"በዓሉን ተከትሎ የህዳሴውን ግድብ ጨምሮ የክልሉ የቱሪስት መስህቦች በተሳታፊዎች ተጎብኝተዋል" ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ "ይህም የክልሉ ሠላም መመለሱን ማሳያ ነው" ሲሉ አክለዋል።

በኢትዮጵያ ቱሪዝምን በማስተዋወቅ ረገድ አዲስ እሳቤ እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ደግሞ የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሌ ናቸው።

"ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሃብቱን በሚገባ ከማወቅ ጀምሮ የአገሩን ገጽታ በማስተዋወቅ በኩል የድርሻውን ማበርከት አለበት" ብለዋል::

በቱሪዝም ዘርፍ የተሠማሩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎታቸውን እንዲያዘምኑ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲና ኮሌጆችም ተግባር ተኮር ትምህርትና ስልጠና እንዲሰጡ አሳስበዋል።

በዚህ ረገድ በተለይም የዲጂታል ዘመኑ የፈጠረውን መልካም አጋጣሚ መጠቀም እንደሚገባ ሚኒስትሯ አስገንዝበዋል።

አንዳንድ የአሶሳ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት "በበዓሉ ክልሉ በሚገባ ተዋውቆበታል" ብለዋል።

የአገር መከላከያ ሠራዊትን ጨምሮ ለበዓሉ በስኬት መጠናቀቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ የፌደራል እና የክልሎች የቱሪዝም እና ባህል ቢሮዎች፣ ባንኮች፣ ሆቴሎችና የጸጥታ አስከባሪ ሃይሎች የእውቅና ሽልማት ተቀብለዋል።

36ኛውን አገር አቀፍ የቱሪዝም ቀን ለማክበር የደቡብ  ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ተመርጧል::

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም