ኢትዮጵያ በፊፋ የዓለም አገራት ወርሃዊ ደረጃ ሁለት ደረጃዎችን አሻሻለች

80
አዲስ አበባ መስከረም 10/2011 ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ በየወሩ ይፋ በሚያደርገው "የፊፋ ኮካ ኮላ" የአገራት እግር ኳስ ደረጃ ኢትዮጵያ ሁለት ደረጃዎችን አሻሽላለች። አገሪቷ ባለፈው ነሐሴ ወር ማህበሩ ባወጣው ደረጃ መሰረት 151ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣ እንደነበር የሚታወስ ነው። በዚህ መስከረም ወር ደግሞ ካለፈው ወር የደረጃ ውጤት ሁለት ደረጃዎችን በማሻሻል ከጓቲማላ እና ከቡሩንዲ በመቀጠል 149ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችላለች። በነሐሴና ጳጉሜ ወራት በሀዋሳ ዓለምአቀፍ ስታዲየም ሁለት ጨዋታዎችን ያደረጉት ዋልያዎቹ በወዳጅነት ጨዋታ ከበሩንዲ ጋር 1-1 በሆነ ውጤት ተለያይተው ነበር። በ2019ኙ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ደግሞ ሴራሊዮንን አስተናግደው 1 ለ 0 ማሸነፋቸው የሚታወስ ነው። በዚህም በወሩ ላሳዩት የደረጃ መሻሻልም በሁለቱ ጨዋታዎች ያስመዘገቡት ውጤት ምክንያት መሆን ችሏል። በዓለም የእግር ኳስ ደረጃ አውሮፓዊቷ አገር ቤልጂየም ቀዳሚውን ደረጃ ስትይዝ የዓለም ሻምፒዮኗ ፈረንሳይ ሁለተኛ፤ የደቡብ አሜሪካዋ ብራዚል ደግሞ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል። ባሃማስ እና ቱርክስ ኤንድ ካይኮስ ደሴቶች የመጨረሻውን 210ኛ ደረጃን የያዙ ሀገራት ናቸው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም