ዩኒቨርሲቲው እንሰትን ለምግብነት ለመጠቀም የሚያስችል የማላመድ ስራ እያካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው እንሰትን ለምግብነት ለመጠቀም የሚያስችል የማላመድ ስራ እያካሄደ ነው
ደብረ ማርቆስ መስከረም 14/2015 (ኢዜአ) የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋር በመተባበር እንሰትን አላማዶ እና አልምቶ ለምግብነት ለማዋል የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ አደረገ።
ቆጮ ወይም እንሰት በደቡቡ የኢትዮጵያ ክፍል በስፋት ከሚታወቁት ተወዳጅና ተመራጭ የምግብ ዓይነት ነው።
በዚያ ልክ በሰሜኑ አጋማሽ የአገሪቷ ክፍል ግን ቅጠሉን ከዳቦ መጋገሪያነት ባለፈ ለምግብነቱ የምሰጠው አገልግሎት እምብዛም ነው።
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ታፈረ መላኩ መድረኩ እንዳሉት የአካባቢው ማህበረሰብ እንሰትን እያለማ ቢኖርም ወደ ቆጮ ቀይሮ ለምግብነት ለማዋል ግን አልለመደም።
ቆጮ ለሰው ልጅ ካለው ዘርፈ ብዙ ጠቃሜታ አንጻር በአማራ ክልል በስፋት እንዲለማ እና እንዲላመድ በማድረግ ለምግብነት ለማዋል ከልማት ባንክ ጋር በመተባበር ስራ መጀመሩን ነው የገለጹት።
ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን የአመጋገብ ባህል በመቀየር በክልሉ በስፋት የሚስተዋለውን የአካባቢ መራቆት የአፈር ለምነት ለማሻሻል ብሎም የህጻናት የመቀንጨር ችግር ለመቀነስ በማሰብ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው በዚህ ዘርፍ በ8 የተመረጡ ወረዳዎች በቀጣይ 10 ዓመታት ተግባራዊ የሚያደርገውን ፕሮጀክት መንደፉን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ፤ በዚህ ዓመት የሚከናወነውን የፕሮጀክቱን ስራ ልማት ባንክ እንደሚያግዝ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዩሐንስ አያሌው በበኩላቸው አገሪቱ የምግብ ዋስትናዋን ለማረጋገጥ ልዩ ትኩረት በሰጠችበት ወቅት ይህ ፕሮጀክት መጀመሩ ፋይዳው የጎላ ነው።
ባንኩ አገሪቱን ከድህነት ሊያላቅቋት የሚችሉ ፕሮጀክቶችን በመደገፍ የበኩሉን አስተዋጽኦ እየተወጣ መሆኑንም አክለዋል።
እንሰትን የማልማት እና የማላመድ ስራ በሁሉም አካባቢዎች እንዲጠናከር ደግሞ ልማት ባንክ በሚችለው አቅም እንደሚደግፍም ቃል ገብተዋል።
የዩኒቨርሲቲው መምህር ባወቀ ጥሩነህ እንዳሉት ቆጮ በሌሎች ክልሎች የተለመደና ተወዳጅ ምግብ ነው፤ ነገር ግን በዚህ አካባቢ ተክሉ ቢኖርም ለምግብነት እየዋለ አይደለም።
በሌሎች አካባቢዎች ያገኙትን ልምድ በመጠቀም ባለፈው አመት በግላቸው በማቻከል ወረዳ በአርሶ አደሮች ጓሮ የሚገኝን እንሰት ፍቀው እና አድርቀው በማስፈጨት ለምግብነት ያዋሉት መሆኑንም ተናግረዋል።
ምግቡንም በፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ በተለያዩ ዝግጅቶች አቅርበው ተሳታፊ አካለት እንዲመገቡት አድርገዋል።
በዚህ አመት ከ3 ሺህ በላይ የእንሰት ችግኞችን በዩኒቨርስቲው የምርምር ማእከላት በማልማት ለገዳማት፣ ለሴቶች እና ለወጣቶች ለመስጠት መታሰቡንም ገልጸዋል።
በተጨማሪም ከ150 ሺህ በላይ የእንሰት ችግኝ በማሰባሰብ ለሚቀጥለው ዓመት ተከላ የሚዘጋጅ መሆኑን አስታውቀዋል።
ህብረተሰቡ ምግብነቱን እንዲለምደውም በትምህርት ቤቶችና በስብሰባ ቦታዎች አዘጋጅቶ በማቅረብ እንዲቀመስ ይደረጋል ብለዋል።
ከዋቻሞ ዩኒቨርስቲ የመጡት እና ስለ እንሰት ጥናታዊ ጽህፍ ያቀረቡት ረዳት ፕሮፌሰር ዳኔል መኖር በበኩላቸው እንሰት ለሰው ልጆች እና ለእንስሳት ምግብነት እንዲሁም ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውል ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ከ20 ሚሊየን ህዝብ በላይ ቆጮን ለምግብነት የሚጠቀም መሆኑን ጥናቶች እንደሚያመላክቱም ተናግረዋል።
እንሰት ድርቅን ከመከላከሉ በላይ በትንሽ ማሳ ብዙ ማምረት እንደሚቻል ገልጸው፤ በሄክታር ከ270 ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ሲሉም አብራርተዋል።
ተክሉ በተተከለ ከ5 እስከ 6 አመት ለምግብነት እንደሚደርስ ጠቅሰው፤ ተፈቅፍቆ ለምግብነት ከተዘጋጀ በኋላም ለሰባት አመት ሳይበላሽ መቆየት እንደሚችል አስረድተዋል።
ፕሮጀክቱን በምስራቅና ምእራብ ጎጃም ዞኖች እንዲሁም በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዱር ቤቴ፣ ኮሶ በር፣ ደንበጫ፣ ፈረስ ቤት፣ ማቸከል፣ ስናን፣ ቢቡኝ እና መርጦ ለማሪያም ወረዳዎች የማልማትና ማለማድ ስራ እንደሚከናወን ታውቋል።
በፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ ፕሮግራም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን በፕሮጀክቱ የ10 ዓመት ቆይታም ከ2 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተመላክቷል።