ቀጥታ፡

የመስቀል ደመራ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ከሕብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት በቂ ዝግጅት አድርጓል

መስከረም 15 / 2015 (ኢዜአ) የመስቀል ደመራ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ከሕብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት በቂ ዝግጅት ማድረጉን አስታወቀ::

የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል የመስቀል ደመራ በዓል በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሃይማኖት አባቶች ጋርም ውይይት አካሂዷል::

የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል::

እንኳን ለመስቀል ደመራ በዓል በሰላም አደረሳችሁ አደረሰንበቅድሚያ የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ለመላው ሕዝበ ክርሰቲያን እንኳን ለ2015 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን እያለ በሀገራችን በየዓመቱ የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኒስኮ ካስመዘገበቻቸው ከማይደሰሱ ቅርሶች ውስጥ አንደኛው ታላቅ በዓል መሆኑ ይታወቃል፡፡

በዓሉ በመላው ሀገራችን በድምቀት የሚከበር ሃይማኖታዊ በዓል ከመሆኑም በላይ የቱሪስት መስህብ በመሆን የሀገራችንን መልካም ገፅታ በመገንባት ረገድ ጉልህ ድርሻ እየተጫወተ ይገኛል፡፡

በመስቀል ደመራ በዓል ላይ መላው ሕዝበ ክርስቲያን በተለይም የእምነቱ ተከታዮች እምነታቸውን በነፃነት በአደባባይ ወጥተው በጋራ የሚያከብሩበት፣ የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን የበለጠ የሚያጠናክሩበት፣ መንፈሳዊ እሴቶቻቸውን የሚያዳብሩበት፣ ተቻችለውና ተከባብረው በጋራ መኖርን ለመላው የዓለም ሕዝቦች ምሳሌ ሆነው የሚታዩበት ታላቅ በዓል ነው፡፡

በመሆኑም የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል የመስቀል ደመራ በዓል በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሃይማኖት አባቶች ጋር ውይይት ያካሄደ ሲሆን ቤተክርስቲያኗን በመወከል በውይይቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ዋና ስራ አስኪያጅና የባህርዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ቤተክርስቲያኗ የ2015 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓልን ለማክበር ከወቅታዊ ሁኔታ አንጻር እጅግ ጥንቃቄ በማድረግ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ማድረጓን ገልፀዋል፡፡

ግብረ-ኃይሉ ከቤተክርስቲያኗ ሥርዓት ውጭ የበዓሉን ድባብ ለማደብዘዝ እና ክብሯን ለመንካት በሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ አስፈላጊውን ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ ሥርዓት እንዲያሲዝ የሃይማኖት አባቶች ጠይቀዋል።ግብረ-ኃይሉም በዓሉ በሰላም እንዲከበር ከሃይማኖት አባቶችና ከሕዝበ ክርስቲያኑ ጋር ተቀናጅቶ ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነት እና ዝግጁነት ለሃይማኖት አባቶች ገልጿል።

ሆኖም የሀገራችንን ሰላምና መረጋጋት የማይፈልገው የህወሓት የሽብር ቡድን ለሦስተኛ ጊዜ የከፈተብንን ጦርነት ተከትሎ የንፁሃንን ህይወት መቅጠፍ የለመደው የኦነግ -ሸኔ የሽብር ቡድን ሰሞኑን በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ይህንኑ እኩይ ተግባሩን ቀጥሎበታል።

የአልሸባብ የሽብር ቡድን እንዲሁም ሌሎች ፀረ-ሰላም ኃይሎች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የሽብር አደጋ ለማድረስ ጥረት እያደረጉ መሆኑንና በዓሉ በሰላም እንዳይጠናቀቅ የተለያዩ የግል አጀንዳዎችን አንግበው የበዓሉን ስነ-ሥርዓት ለማወክ የተዘጋጁ ኃይሎችም እንዳሉ ግብረ-ኃይሉ ደርሶበታል፡፡

በመላው ሀገራችን በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ከሕብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት በቂ ዝግጅት በማድረግ ስምሪት ወስዶ እየሰራ እንደሚገኝና በሽብር ኃይሎች ላይ እየወሰደ ያለውን ጠንካራ እርምጃም አጠናክሮ ይቀጥላል።

ስለሆነም በሃይማኖት ሽፋን የፖለቲካ አጀንዳዎችን ማራገብና ማንፀባረቅ ተገቢ እንዳልሆነ ሁሉም ተገንዝቦ ከበዓሉ ሥነ-ስርዓት ውጪ ግጭት ቀስቃሽ ጽሁፎች እና ማንኛውንም ሁከት ቀስቃሽ ነገሮችን በማንኛውም ሁኔታ በዓሉ ወደ ሚከበርበት ቦታ ይዞ መምጣት በጥብቅ የተከለከለ መሆኑን ግብረ-ኃይሉ እየገለፀ ይህንን ክልከላ ተላልፈው የበዓሉን ድባብ ለማደብዘዝ በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ጥብቅ ሕጋዊ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን ከወዲሁ ያሳውቃል።

በተጨማሪም የመስቀል ደመራ በዓል ከሚፈቅደው ስነ-ስርዓት ውጪ በበዓሉ ድባብ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ለመፍጠር የሚደረግ ማንኛውም ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል ስለሆነ የሃይማኖት አባቶች፣ የየደብሩ አስተዳደሮች፣ በዓሉን በኮሚቴነት የምታስተባብሩና የምትመሩ አካላት፣ ሕዝበ ክርስቲያን እንዲሁም የሀገራችን ወጣቶች ከፀጥታ አካላት የሚሰጠውን መመሪያ ከግምት ውስጥ በማስገባት በዓሉ በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ እንድታደርጉ ግብረ-ኃይሉ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የበዓሉ ታዳሚዎች የበዓሉን ሥነ-ስርዓት የሚያውክ የተለየ እንቅስቃሴ ስትመለከቱ በአቅራቢያችሁ ለሚገኙ የፀጥታ አካላት መረጃ በመስጠት የተለመደ ትብብራችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ጥሪውን እያስተላለፈ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ በድጋሚ በዓሉ የሰላም የፍቅር የአንድነትና የደስታ እንዲሆንላችሁ ይመኛል፡፡

መልካም በዓል!!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም