ቀይ መስቀል ማህበር በጸጥታ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ቀይ መስቀል ማህበር በጸጥታ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አደረገ
መስከረም 15/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ተፈናቅለው በመተማ ወረዳ ለሚገኙ ወገኖች ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን በማህበሩ የምዕራብ ጎንደር ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ አስተባባሪ አቶ ግዛቸው በለጠ እንደተናገሩት ድጋፉ ከኢትዮጵያና ከዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ማህበር የተገኘ ነው።
ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በፀጥታ ችግር ምክንያት የተፈናቀሉና በአካባቢው የነበሩ ወገኖችን በመደገፍ ማህበሩ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ሲወጣ መቆየቱን አስታውሰዋል።
የአሁኑ ድጋፍ የተደረገው ከ2013ዓ.ም ጀምሮ በኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በፅንፈኞች በተካሄደ የፀጥታ ችግር ተፈናቅለው በመተማ ወረዳ ለሚገኙ 360 ወገኖች ነው።
ደጋፉ ከተደረገላቸው መካከል አቶ ሰዒድ አሊ እንዳሉት ''ይህ ድጋፍ መንግስትና ረጅ ድርጅቶች በፈተና ውስጥም ሆነው ዜጎችን ማየት የሚችሉ መሆኑን ያሳየ ነው'' ብለዋል።
አሁን ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው፤ በቀጣይ መሰል ድጋፎች እንዲደረጉላቸው ጠይቀዋል።
ሌላኛዋ የድጋፉ ተጠቃሚ ወይዘሮ ስመኝሽ ዘውዱ በበኩላቸው የተደረገላቸው የገንዘብ ድጋፍ የእለት ችግራቸውን የሚቀርፍ በመሆኑ ማህበሩን አመስግነዋል።
''ዛሬ 6 ሺህ 500 ብር ድጋፍ ተደርጎልኛል ያሉት ወይዘሮ ስመኝሽ ይህም ከልመና ለመውጣት በአነስተኛ የገቢ ማስገኛ ስራ ለመሰማራት ያስችለኛል" ብለዋል።
ተፈናቃዮችን በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ምላሽ ቡድን መሪ አቶ ዘላለም አበበ ናቸው።
በፀጥታ ችግር ምክንያት ከሌሎች አካበቢዎች የተፈናቀሉ ከ7 ሺህ በላይ ወገኖች በአካባቢው እንዳሉ ጠቅሰው፤ አቅም በፈቀደ መጠን መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በማስተባበር የእለት ድጋፍ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።