የህዝቡን ቱባ ባህሎች በጥናትና ምርምር በማበልጸግ በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ ተጠቆመ

አርባ ምንጭ መስከረም 14/2015 (ኢዜአ)----ያልተነኩና ያልተዳሰሱ የህዝብ ቱባ ባህሎችን በማበልጸግ በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውሉ በጥናትና ምርምር መደገፍ ይገባል ሲሉ የደቡብ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ጥላሁን ከበደ አስገነዘቡ።

“ዱቡሻ” የተሰኘው የጋሞ ባህላዊ የሸንጎ ስርአትን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ተገልጿል።

የጋሞ ብሔር የዘመን መለወጫ “ዮ…ማስቃላ” በዓል የተለያዩ አካላት በተገኙበት በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ተከብሮ ውሏል።

በበዓሉ ላይ የተገኙት የክልሉ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ጥላሁን ከበደ “ዮ…ማስቃላ” በጋሞ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል ከመሆኑም በላይ የደስታና የአብሮነት መገለጫ መሆኑንም ተናግረዋል።

"የጋሞ ህዝብ የሰላም፣ የፍቅር እና የአቃፊነት ተምሳሌት እንደሆነ ጥንት አያቶቻችንና አባቶቻችን ያቆዩትን ታሪክ ለመጪው ትውልድ ማቆት ይገባናል" ሲሉም አስገንዝበዋል።

ዘመናዊ የአስተዳደር ስርአት ባልተጀመረበት ጊዜም የጥንት አባቶች በባህላዊ ስርአት ትውልድን እያነጹ መቆየታቸውን አውስተዋል።

በጋሞ ዞን የጋሞ፣ የዘይሰና ጊድቾ ብሔረሰቦች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ "የእነዚህ ህዝቦች ያልተነኩና ያልተዳሰሱ በርካታ ቱባ ባህሎች በመኖራቸው በጥናትና ምርምር በማስደገፍ ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል" ብለዋል

ህዝቡ ባህሉን እንዲያሳድግ፣ እንዲያበለጽግና ጥቅም ላይ እንዲያውል መንግስት የቀረጸውን የባህል ፖሊሲ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

"ባህላችን ቢጠፋ ተጠያቂዎች እኛው ራሳችን ነን" ያሉት አቶ ጥላሁን፣ ባህሉ ሳይበረዝ ለትውልድ የማቆየት ታሪካዊ ሃላፊነትን በአግባቡ መወጣት እንደሚገባ አመልክተዋል።

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ ባህሎች የህዝቡን አንድነት ከማጠናከርም በላይ ችግሮችን በመፍታት ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው ገልጸዋል።

"ለባህላችን ትኩረት ባለመስጠታችን ባህላችን እየተሸረሸረና ሰዉም የተፈጥሮ ማንነቱን እያጣ በመሆኑ ለባህላችን ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል" ብለዋል።

ቱባ ባህሎች ለትዉልዱ እንዲተላለፉ ፋይዳውን በማስገንዘብ አባቶች ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አመልክተዋል።

ባህሎችን በጥናትና ምርምር ለማበልጸግ በሚደረገው ጥረት መንግስት አስፈላጊዉን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

ጋሞ ዞን የባህል፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖት ብዝሃነትና የተፈጥሮ መስህቦች ባለፀጋ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የጋሞ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ አቶ ሙናዬ ሞሶሌ ናቸው።

ቋንቋና ባህልን በማበልጸግ ለሳይንስና ቴክኖሎጂለመጠቀም ብዙ መስራት ይጠበቅብናል" ብለዋል።

“ዱቡሻ” ስለተሰኘው የጋሞ ባህላዊ የሸንጎ ስርአትን ለአሁኑ ትውልድ ግንዛቤ ከመፍጠርም በላይ በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

“ፈተናዎችን በመቋቋም ባህላዊ እሴቶችን እናበለጽጋለን” በሚል መሪ ሃሳብ በ”ዱቡሻ” ባህላዊ የእርቅ ስነ-ስርአት እና ”ዮ…ማስቃላ” በዓል ፋይዳዎችን በተመለከተጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ዉይይት ተደርጎባቸዋል።

በተጨማሪም በበዓሉ ላይ የጋሞ ህዝብ ባህላዊ ቁሶችና የጥበብ ውጤቶች በአውደርዕይ የቀረቡ ስሆን የጋሞ የሰላም ተምሳሌት ምልክት የሆነው ሀውልትም ተመርቋል

በዓሉ በነገው ዕለትም በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሮ እንደምውል ከዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም