ቤተ-እምነቶችን ማውደምና ለጦር መሳሪያ ማከማቻ ማዋል የዜጎችን እሴት ለማጥፋት የሚደረግ የኢትዮጵያ ጠላቶች ሴራ ነው--የሃይማኖት አባቶች

93

መስከረም 14/2015/ኢዜአ/ ቤተ-እምነቶችን ማውደምና ለጦር መሳሪያ ማከማቻ ማዋል የዜጎችን እሴት ለማጥፋት የሚደረግ የኢትዮጵያ ጠላቶች ሴራ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው ሃይማኖት አባቶች ተናገሩ።

ኢትዮጵያ ታሪኳንና እሴቷን ሊያጠፉ በየዘመናቱ የተነሱ የውጭ ጠላቶችና ባንዳዎችን በመመከት በወርቅ መዝገብ የተተከለ አኩሪ ታሪክ አላት።

በዚህም ብዝሃ ማንነት ያላቸው ዜጎች መገለጫ የሆኑ እሴቶቻቸውን ጠብቀውና አንድነታቸውን አጠናክረው ለዘመናት በጋራ ኖረዋል፡፡

ይህም ኢትዮጵያን ብዝሃ ማንነት ውስጥ ያለ የመቻቻልና የመከባበር አብነት አድርጓታል፡፡

ነገር ግን በቀጥታ ፊት ለፊት በጦርነት መጥተው ያልተሳካላቸው የኢትዮጵያ ጠላቶች የአገር ውስጥ ባንዳዎችን በመጠቀም የኢትዮጵያዊያን መገለጫ የሆኑ እሴቶችን በማጥፋት አገር ለማፍረስ እየሞከሩ ይገኛሉ፡፡

አሸባሪው ህወሓት የፈጸማቸው እኩይ ተግባራት ደግሞ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነው፡፡

አሸባሪ ቡድኑ ቤተ-እምነቶችን ምሽግ በማድረግ፣ በማፈራረስና አጸያፊ ተግባር በመፈጸም የዜጎችን የማንነት እሴቶች ለማጥፋት የሚደረግ የኢትዮጵያ ጠላቶች ሴራ አካል መሆኑን በተግባር አረጋግጧል፡፡

ቅዱስ ቁርአንን እና መጽሐፍ ቅዱስን በመቅደድ በታሪክም ይሁን በመንፈሳዊ ህይወት እጅግ ይቅር የማይባል ተግባር መፈጸሙን ነው ከዚህ ቀደም ኢዜአ ያነጋገራቸው የሃይማኖት አባቶች የገለጹት፡፡

በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢ ወረራ በፈጸመበት ወቅትም በቤተ- እምነቶች ላይ እጅግ አስነዋሪ ተግባር መፈጸሙን  በወቅቱ የነበሩ የእምነት አባቶች መናገራቸው ይታወሳል።

በቅርቡ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሃይማኖት አባቶች በበኩላቸው ምንም የፖለቲካም ሆነ ሌሎች ልዩነቶች ቢኖሩን ቤተ -እምነቶች ማፍረስና ለሌሎች ተግባራት ማዋል በፈጣሪ ይቅር የማይባል ተግባር ነው ይላሉ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቅርስ ጥበቃና ቤተ- መፃህፍት ወመዘክር መምሪያ ዋና ኃላፊ መላከ ሰላም ቆሞስ ዶክተር አባ ቃለጽድቅ ሙሉጌታ፤ የኢትዮጵያን አንድነት የማይፈልጉ ጠላቶች የውስጥ ባንዳዎችን በመጠቀም እርስ በእርስ ለማጣላት እንደሚሰሩ ይናገራሉ፡፡

ይህን እኩይ ተግባራቸውን ለማሳካት ደግሞ ቤተ- እምነቶችን ማቃጠልና ታሪክን ማጥፋት ቀዳሚ አጀንዳቸው አድርገው እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አሸባሪው ህወሃት የፈጸመውም ይህንኑ ተግባር መሆኑን በመጠቆም፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ በበኩላቸው ቤተ -እምነቶች የሰው ልጅ ለፈጣሪው ምስጋና የሚያቀርቡባቸው ክቡር ስፍራዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ቤተ-እምነቶችን ማቃጠል በፈጣሪ የሚያስጠይቅ ወንጀል መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን በመከባበርና አንድነታቸውን በመጠበቅ ሊከፋፍሏቸው የሚፈልጉ ጠላቶችን ሴራ ማክሸፍ እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም