የወላይታና ሲዳማ ህዝቦችን ያስተሳሰሯቸው ባህላዊ እሴቶች ጠንካራ ናቸው - የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር

116

ሶዶ መስከረም 14/2015 /ኢዜአ/ የወላይታና ሲዳማ ህዝቦችን ያስተሳሰሯቸው ባህላዊ እሴቶች ጠንካራ በመሆናቸው አሸባሪው ህወሓት ልዩነት ለመፍጠር የወጠነው ሴራ እንዲከሽፍ ማስቻሉን የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ገለጹ።

የሲዳማ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሀላፊ በበኩላቸው፤ ሁለቱ ህዝቦች ከባህላዊ እሴቶች በተጨማሪ በጋብቻ የተዛመድን መሆናችን ሊለየን የሚችል ምንም አይነት ምክንያት የለም ብለዋል።  

የወላይታ ብሄር ዘመን መለወጫ በዓል “ጊፋታ”ን ምክንያት በማድረግ ዛሬ በሶዶ ከተማ በተካሄደው ሲምፖዚየም ላይ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕስ መስተዳድር አቶ ተስፋዬ ይገዙ በተለይ ለኢዜአ እንዳሉት፤ “ጊፋታ” በህዝቦች መካከል አንድነት፣ መረዳዳትና መተባበርን የሚያጠናክር በዓል ነው።

“በዓሉ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን፣ ወንድማማችና እህትማማችነትን ለማጠናከርና ለማጎልበት የሚያስችል እሴቶችን የያዘ ነው” ብለዋል።

“ጊፋታ” የይቅርታ፣ የፍቅር፣ የአብሮነትና አንድነት፣ መረዳዳት፣ ውጤታማ ለመሆን በስራ መትጋትንና መሰረት ያደረጉት እሴቶቹ በዓሉ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር በጋራ እንዲያከብር ያደረጉት መሆኑን አስረድተዋል።

ከለውጡ በፊት አሸባሪው ህወሓት በደቡብ ክልል የሚገኙ ህዝቦች ያነሱት የነበረውን የመዋቅር ጥያቄ በማፈንና ይህን በመጠቀም በብሄሮች መካከል ቅራኔና ቁርሾ ሲፈጥርበት መቆየቱን ጠቁመዋል።

በዚህም በወላይታና በሲዳማ ህዝቦች መካከል ቅራኔ በመፍጠር እርስ በእርስ ግጭት በመፍጠር ለማራራቅ ያደረገው ሙከራ በሁለቱ ህዝቦች ያሉ እሴቶችን በመጠቀም መፍታት እንደተቻለ ገልጸዋል።

“ሲዳማና ወላይታ በኩታ ገጠም ወሰን የሚጋሩና ያስተሳሰሯቸው ባህላዊ እሴቶች ጠንካራ በመሆናቸው አሸባሪው ያሰበውና የፈለገው ሳይሳካለት እንዲቀር አድርጓል” ብለዋል።

የሲዳማ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሀላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዮስ በበኩላቸው፤  ሲዳማና ወላይታ ካላቸው አንድ የሚያደርጓቸው እሴቶች በተጨማሪ በጋብቻ የተሳሰሩ መሆናቸው አሸባሪው  ህወሀት ያሰበው ሴራ በአጭሩ እንዲቋጭ ምክንያት ሆኗል ብለዋል።

ለ27  ዓመታት ስልጣን ላይ የነበረው አሸባሪው ህወሓት የስልጣን ዕድሜውን ለማራዘም ልዩነትን በመጠቀም እርስ በእርስ ለመከፋፈልና ለማጋጨት በስውርና በግልጽ ሲሰራ ቢቆይም ሳይሳካለት መቅረቱን ገልጸዋል።   

ለውጡ ያመጣውን ህብረ ብሄራዊ አንድነት መሰረት በማድረግ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ባለፉት ስርዓቶች የተፈጠሩ ቁርሾዎችን በማረም አብሮነትን በማጠናከር በመረዳት፣ በፍቅርና በመተሳሰብ መኖር እንደቻሉ አብራርተዋል አቶ አለማየሁ።

አሸባሪው ህወሀት አንዱን ከአንዱ በማጋጨት ትርፍ ለማግኘት በማሰብ ሁለቱን ህዝቦች ለመለያየት ቢሞክርም በሀገር ሽማግሌዎች ችግሩን በመፍታት ዛሬ በጋራ በዓላችንን ለማክበር ችለናል ነው ያሉት ደግሞ የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ ለማ ናቸው።

“የጊፋታ በዓል ሲከበር በጋራና በአብሮነት በመሆኑ ከሲዳማ ወንድም እህቶቻችን ጋር በመሆን ደስ በሚያሰኝ መልኩ አዲሱን አመት እየተቀበልን ነው” ብለዋል።

የወላይታ ዘመን መለወጫ በዓል ጊፋታን ምክንያት በማድረግ ዛሬ በወላይታ ሶዶ ከተማ የሶስት ኪሎሜትር ሩጫ ውድድርና የባህልና የቋንቋ ሲምፖዚየም የተካሄደ ሲሆን፤ ነገ አዲሱን ዓመት አንድ ብለው የሚጀምሩበት ሥነ-ሥርዓት በአደባባይ እንደሚካሄድ የኢዜአ ሪፖርተር ከሥፍራው ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም