የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ስኬት ለማስቀጠል የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ያስፈልጋል

58
አዲስ አበባ መስከረም 10/2011 የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ስኬት ለማስቀጠል የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ ተገለፀ። በሳዑዲ ዓረቢያ አዲስ የተሾሙት የኢትዮጵያ አምባሳደር አብዱልአዚዝ አህመድና በጂዳ የኢትዮጵያ ቆንስል ጄኔራል አብዱ ያሲን ከኤምባሲውና ከቆንስላው ሰራተኞች ጋር ውጤታማ የዲፕሎማሲ ስራ መስራት በሚቻልበት ዙሪያ ተወያይተዋል። አምባሳደር አብዱልአዚዝ በውይይቱ ወቅት እንዳሉት ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎችን ለመከወን ከውጭ ግንኙነት ሰራተኞች ባለፈ ሁሉም ዜጋ የአገሩ አምበሳደር መሆን አለበት። ዘመናዊ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴን በመከተል ዳያስፖራውንና ሌሎች ደጋፊ አካላትን ማሳተፍም ይገባል ብለዋል። አምባሳደሩና ቆንስል ጄኔራሉ በኒው ጂዳ በሚባል ሆስፒታል ተገኝተው ሀዚም ይማም የተባለን ታዳጊ ጎብኝተዋል፤ ከሳዑዲ መንግስት ጋር በመሆን አስፈላጊው ክትትል እንደሚደረግለትም ገልጸዋል። ኤምባሲው ቀደም ሲል በህክምና ስህተት ጉዳት የደረሰበት ኢትዮጵያዊ ታዳጊ ሞሀመድ ካሳ ተከፍሎት ወደ አገሩ እንዲመለስ ማድረጉ ይታወቃል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ታዳጊውን መጎብኘታቸውም ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም