የኢትዮጵያ ሠላም ዘላቂ ለማድረግ አሸባሪዎቹ ህወሃትና ሸኔ ሊወገዱ ይገባል - በአሸባሪዎቹ የግፍ ሰለባ የሆኑ ተፈናቃዮች

19

አሶሳ፤ መስከረም 14 / 2015 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ሠላም ዘላቂ ለማድረግ አሸባሪዎቹን  ህወሃትና ሸኔ ማስወገድ እንደሚገባ በአሸባሪዎቹ የግፍ ሰለባ የሆኑ ተፈናቃዮች ተናገሩ፡፡

አሸባሪው ህወሃት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማህበረሰብ ከ2011 እስከ 2013 ዓ.ም. በዘር እና ቀለም ለያይቶ በማጋጨት ባደረሰው ጥፋት በርካታ ወገኖች ህይወታቸውን አጥተዋል፤ ከፍተኛ ግምት ያለው ንብረት መውደሙንና  ነዋሪዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡

በክልሉ ከካማሺ ዞን ለ22 ዓመታት ከኖሩበት ሰዳል ወረዳ እንደተፈናቀሉ የተናገሩት ቄስ አዲሱ አባት በአሸባሪው ህወሃት ቅጥረኞች የደረሰባቸውን ግፍ ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

በሽብር ቡድኑ የጥፋት አስፈጻሚዎች በርካታ ንጹሃን ታርደው ጭምር መገደላቸውን ፤ ፈርተው ሲሸሹ የነበሩ ወላድ እናቶች በህክምና ድጋፍ እጦት በየመንገዱ ሲወልዱ መመልከታቸውን አስታውሰዋል፡፡

ግጭት ተከስቶ በነበረበት ወቅት በአካባቢው የሚገኙ የጸጥታ አስከባሪ ሃይሎች ያለልዩነት ህብረተሰቡን ለማዳን ርብርብ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡

እርሳቸው ጨምሮ ከአካባቢው የተፈናቀሉ እንዳይገደሉ የጉሙዝ ማህበረሰብ   ከለላ በመስጠት ኢትዮጵያዊ ወገንተኝነታቸውን ማሳየታቸውን የገለጹት  አስተያየት ሰጪው፤  እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ጥፋት ተፈጽሞባቸዋል ብለዋል፡፡

ወይዘሮ ሃዋ ጃለታ በበኩላቸው፤ በካማሺ ዞን ሰዳል ወረዳ አስተዳደር ጽህፈት ቤት በጸሐፊነት ሲሰሩ እንደነበርና  በሽብር ቡድኑ የግፍ ድርጊት ተፈናቅለው ሶስት ልጆቻቸው ይዘው ወደ አሶሳ ከተማ መሰደዳቸውን ተናግረዋል።

ለወራት የቤት ኪራይ ባለመክፈላቸው ከነ ልጆነቻቸው ለእንግልት መዳረጋቸውን አስረድተዋል፡፡

ከኦሮሚያ ክልል መንዲ ወረዳ ተፈናቅለው በባምባሲ መጠለያ የሚገኙት  ወይዘሮ የማታ ሞላ ፤ በግብርና ስራ ራሳችንን ከመቻል አልፈን ሌሎችን እንረዳ ነበር ብለዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ ባደረሰው ጥፋት ለተረጂነት ተጋልጠናል ሲሉ በቁጭት ገልጸዋል፡፡

ችግሩ በተለይም በወላድ እናቶች እና በህጻናት ላይ የከፋ መሆኑን ጠቅሰው፤ ህብረተሰቡ ባደረገው ምግብና ሌሎች ድጋፎች ተስፋችንን አለምልሞታል ብለዋል፡፡

ሰርቼ ራሴን በምቀይርበት የወጣትነት ዘመኔ ተረጂ እንድሆን ያደረጉኝ ሽብርተኞቹ ህወሃት እና ሸኔ ናቸው ያሉት ደግሞ  ባቦገምቢል ወረዳ የተፈናቀለው ወጣት ዘነበ መኮንን ነው፡፡

ሰርቶ ራሱን በመቀየር ከተፈናቃይነት ህይወት የመላቀቅ ህልም እንዳለው ወጣቱ ገልጾ፤ እቅዴ የሚሳካው ግን ኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላሟ ሲረጋገጥ ነው፤ ለዚህ ደግሞ  ጁንታው እና ሸኔን ተባብረን ማስወገድ የግድ ነው ብሏል።

የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሃይማኖት ዲሳሳ እንዳስረዱት፤ ዩኒቨርሲቲው በክልሉ በተከሰተው ግጭት ላይ ጥናት ለማድረግ ሞክሯል፡፡

ጥናቱ በክልሉ በአብዛኞቹ መተከል፣ ካማሺ እና አሶሳ ዞኖች እንዲሁም ማኦ ኮሞ ልዩ ወረዳ እንደሸፈነ ጠቁመዋል፡፡

ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ የክልሉ ነዋሪዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን ጥናቱ እንደሚያመላክት ጠቁመው፤ ከ71 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የግለሰብ እና የመንግስት ተቋማት ንብረቶች እንዲሁም መሠረተ ልማቶች መውደማቸውን አብራርተዋል፡፡

ግጭቱ የክልሉ ህዝብ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ አቅሙ እንዲዳከም እና ጠባቂ እንዲሆን ማድረጉን ጥናቱ ማመላከቱን ዶክተር ሃይማኖት ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ጥናቱን ሙሉ በሙሉ ሲያጠናቅቅ ጉዳዩን በዝርዝር ይፋ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡

ከጥናቱ በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲው አቅሙ በፈቀደ ተፈናቃዮችን በገንዘብ እና በዓይነት ለመደገፍ የድርሻውን ለመወጣት ጥረት እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አደጋ ስጋት እና ስራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ታረቀኝ ታሲሳ፤  በክልሉ በግጭት ከተፈናቀሉ መካከል ከግማሽ በላይ የመተከል ዞን ነዋሪዎች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

199 ጤና ተቋማት ከነቁሳቁሳቸው፣ 287 አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ 53 ወፍጮዎች፣ 340 የግብርና ማሰልጠኛ እና የእንስሳት ህክምና መስጫ ተቋማት ሙሉ በሙሉ እና በከፊል መውደማቸውን ጠቅሰዋል፡፡

86 አምቡላንስ፣ ዶዘር እና ትራክተሮች እና ከ43 ሺህ በላይ የግለሰቦች መኖሪያ ቤቶች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል ብለዋል፡፡

የክልሉ እና የፌደራል መንግት እንዲሁም ህብረተሰቡ ባደረገው የጋራ ርብርብ በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የክልሉ አካባቢ አንጻራዊ ሠላም እየሰፈነ መምጣቱን ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል፡፡

ያለውን ሠላም በመጠቀም ከአጠቃላይ ተፈናቃዮች መካከል 269 ሺህ ያህሉን ወደ ቀያቸው መመለስ መቻሉን ጠቀመዋል፡፡

የግብርና ግብአቶችን በማቅረብ የእርሻ ስራ የጀመሩ ተፈናቃዮች እንዳሉ  አብራርተዋል፡፡

የክልሉ መንግስት  ተፈናቃዮችን በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም ስትራቴጂክ እቅድ ማዘጋጀቱን አቶ ታረቀኝ አመልክተው፤ መልሶ ማቋቋሙ ከ38 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም