የደቡብ ኦሞ ዞን ለመከላከያ ሠራዊት ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የደቡብ ኦሞ ዞን ለመከላከያ ሠራዊት ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገ
መስከረም 14/2015/ኢዜአ/ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል የደቡብ ኦሞ ዞን የኢትዮጵያን ሉዓላዊ አንድነት በማስጠበቅ ላይ ለሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የአይነት ድጋፍ አደረገ።
ድጋፉንም በደቡብ ክልል የደቡብ ኦሞ ዞን የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ ሎቱሩስ ካረ ለመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታዋ ማርታ ሉዊጂ አስረክበዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ ማርታ ሉዊጂ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የደቡብ ኦሞ ህዝቦች ለሰራዊቱ እያደረጉት ያለውን ድጋፍ አድንቀዋል፡፡
በቀጣይም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና አንድነት ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት ላይ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ለሰራዊቱ ያላቸውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም እንዲሁ፡፡
የኢትዮጵያን ሉዓላዊ አንድነት ለማስቀጠል በቁርጠኝነት እየታገለ ለሚገኘው ጀግናው ሰራዊታችን ላበረከታችሁት አስተዋጽኦም ክብር አለን ሲሉ ገልጸዋል።
በቀጣይም የዞኑ ወጣቶች የአገር መከላከያ ሰራዊትን በመቀላቀል የሰለጠነና የተማረ የሰራዊት አባል ሆነው የኢትዮጵያን ሉዓላዊ አንድነት አስጠብቀው እንዲያስቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የደቡብ ኦሞ ዞን የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ ሎቱሩስ ካረ፤ የዞኑ ህዝብ በድንበር አካባቢ ከመኖሩ ጋር ተያይዞ ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የጸረ-ሰላም ኃይሎችን እንቅስቃሴ ለመመከት እየሰራ አንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጠላቶችን እየተፋለመ ለሚገኘው የአገር መከላከያ ሰራዊት ደጀንነቱን ለማሳየት የዞኑ ነዋሪዎች ከ7 ሚሊዮን 136 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የአይነት ድጋፍ አድርገዋል ብለዋል።
ድጋፉም ለሶስተኛ ጊዜ የተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአጭር ጊዜ በተከናወነ ስራ 165 ሰንጋ፣ 274 በግና ፍየል እንዲሁም በሶ፣ ቆሎና ሌሎች የደረቅ ሬሽን ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በአራቱም ማዕዘን ያሉ ኢትዮጵዊያን ለአገር ሉዓላዊነትና አንድነት አኩሪ ተጋድሎ እያደረገ ለሚገኘው ጀግናው የመካለከያ ሰራዊት እያደረጉት ያለው የደጀንነት ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል።