ቀጥታ፡

ለአገር መከላከያ ሠራዊት የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን...በቻይና ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን

መስከረም 14/2015 (ኢዜአ) በቻይና የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለመከላከያ ሠራዊትና በችግር ላይ ለሚገኙ ወገኖች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናገሩ ።

በቻይና የኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ማኅበር ሊቀመንበር አቶ አስቻለው በላይ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ለአገር መከላከያ ሠራዊት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

የአገርን ሉዓላዊነትና አንድነትን ለማስጠበቅ ለሚዋደቀው የአገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ማድረግ የዜግነት ኃላፊነት መሆኑን ጠቁመው አሸባሪው የሕወሃት ቡድን በአገሪቱ ላይ የደቀነውን አደጋ መከላከል የሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ በጦርነቱና በሌሎቹ አደጋዎች ችግር ላይ ለወደቁ የማኅበረሰብ ክፍሎችም እንደ ግለሰብም እንደ ማኅበር ድጋፍ የማሰባሰብና የመደገፍ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።  

  በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ በበኩላቸው በቻይና የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለመከላከያ ሠራዊትና በችግር ላይ ለሚገኙ ወገኖች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በቻይና ዋና ከተማ ቤጂንግ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የዳያስፖራው ተሳትፎ በተመለከተ ውይይት ተደርጓል።

ከውይይቱ ጎን ለጎን ለአገር መከላከያና ችግር ላይ ለወደቁ የማኅበረሰብ ክፍሎች የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ተካሂዷል።

በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ  በዚህ ወቅት አሸባሪው ሕወሃት መንግስት በተደጋጋሚ የዘረጋውን የሰላም መንገድ ወደ ጎን በመተው ለሶስተኛ ጊዜ ጦርነት መክፈቱን ተናግረዋል፡፡

በዚህም በርካታ ኀብረተሰብ ክፍሎችን ለአላስፈላጊ እንግልት እየዳረገ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

መንግሥት ለሰላም የዘረጋውን እጅ እንደማያጥፍ የጠቆሙት አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ፤ ከዚህ አኳያ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኢትዮጵያ መንግስት ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ሊገነዘብ ይገባል ነው ያለት፡፡

እንዲያም ሆኖ መንግሥት በሕዝብ የተጣለበትን አገርንና ሕዝብን የመጠበቅ ተግባር በብቃት እየተወጣ መሆኑን ገልጸው ከዚህ አኳያ ለመከላከያ ሰራዊቱ ድጋፍ  እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመሆኑም በቻይና የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለመከላከያ ሠራዊት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ነው ያለት፡፡

"ያለችን አንድ አገር ነች"ያሉት አምባሳደሩ ሁሉም በአቅሙ አገሩን በማገዝ የዜግነት ግዴታውን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ ችግር ላይ የወደቁ ወገኖችን መደገፍና መልሶ የማቋቋሙ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም