ተቋማት የአካል ጉዳተኞች የስራ ስምሪት መብት አዋጅ ላይ የተቀመጡ ተጠቃሚነቶችን በአግባቡ እየተገበሩ እንደማይገኝ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ተቋማት የአካል ጉዳተኞች የስራ ስምሪት መብት አዋጅ ላይ የተቀመጡ ተጠቃሚነቶችን በአግባቡ እየተገበሩ እንደማይገኝ ተገለጸ
መስከረም 14 2015 (ኢዜአ) የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የአካል ጉዳተኞች የስራ ስምሪት መብት አዋጅ ላይ የተቀመጡ የስራ እድል ተጠቃሚነቶችን በአግባቡ እየተገበሩ አለመሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ተቋማትና ማህበረሰቡ በአካል ጉዳተኞች ላይ ያላቸውን የተዛቡ አመለካከቶችና ባህሎች አስመልክቶ የተዘጋጀ የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ ዛሬ በአዳማ ተጀምሯል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ተግባራዊ የሚያደርገው የአካል ጉዳተኞች የስራ ስምሪት መብት አዋጅ ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ በስራ ላይ ይገኛል።
በአዋጅ ቁጥር 568/2000 አካል ጉዳተኞች በሰራተኞች ምልመላና ቅጥር ላይ ተመጣጣኝነትን ማመቻቸት፣ያልተገባ ጫና አለመፍጠር፣በአነሰ ሁኔታ አለማስተናገድና ልዩነት አለማድረግ እንደሚገባ ያስቀምጣል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞች ማስተዋወቅና መብት ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ሲሳይ ጥላሁን መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በአዋጁ አማካኝነት አካል ጉዳተኞችን በሚፈለገው መጠን ወደ ስራ እያስገቡ አይደለም ብለዋል።
ይህም የሚመነጨው ተቋማት ሕጉን በሚገባ ባለማወቃቸውና ካለመረዳት እንደሆነ ገልጸዋል።
በአዋጁ ተቋማት ከተጣለባቸው ኃላፊነት የተነሳ የአካል ጉዳተኞችን የስራ እድል ተጠቃሚነት ሊያሳድጉ እንደሚገባ አመልክተዋል።
የትምህርት ተቋማትም ለአካል ጉዳተኛ ሕጻናት አመቺ የሆኑ መሰረተ ልማቶች ሊኖራቸው ይገባል ነው ያሉት አቶ ጥላሁን።
የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ በሁሉም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና ተጠሪ ተቋማት እቅዶችና ፕሮግራሞች እንዲካተቱ መደረጉንና ለትግበራውም ከተቋማቱ ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን የአካል ጉዳተኞች መብቶችና አቅም ግንባታ ፕሮጄክት አስተባባሪ ወይዘሮ ስምረት ዘነበ መንግስት አካል ጉዳተኞችን በትራንስፖርት፣ጤና እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ፕሮጀክቶችና እቅዶች አሳታፊ ማድረግ የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎችን በማውጣት እያከናወነ ያለው ተስፋ ሰጪ ስራ ይበልጥ መጠናከር አለበት ብለዋል።
ሕብረተሰቡና ተቋማት ስለ አካል ጉዳተኝነት ያላቸው አመለካከትና ባህል ያለመለወጥ መብትና ጥቅማቸውን በሚፈለገው መልኩ ከማስጠበቅ አንጻር ያሉ ተግዳሮቶች ዛሬም አጥጋቢ መፍትሔ አለማግኘታቸውን የገለጹት ደግሞ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ብሔራዊ ማህበር ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ምህረት ንጉሴ ናቸው።
በመንግስት የሚከናወኑ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችና የልማት ስራዎች እንዲሁም የተግባቦትና የመረጃ ተደራሽነት ችግር እንዲሁም የምልክት ቋንቋ፣ስዕላዊ መግለጫዎችና ብሬኖች አለመሟላት አሁንም በዘርፉ የሚታዩ ችግሮች ናቸው ብለዋል።